በሴካፋ ውድድር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ሲደረጉ በመጀመሪያው ጨዋታ ዩጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻ ተለያይተዋል። በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ጂቡቲ እና ኬንያን ተገናኝተው ኬንያ 3-0 አሸንፋለች።
👉ዩጋንዳ 0-0 ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
በመክፈቻው ቀን እንደሚደረግ ቀድሞ የተነገረው የዩጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋታ በተጋባዧ ሀገር ዘግይቶ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ምክንያት ወደ ዛሬ ተዘዋውሮ እንደነበር ይታወሳል። ጨዋታውም 7 ሰዓት ሲል ተጀምሯል። በጨዋታው ዩጋንዳዎች በተሻለ ከኳስ ጋር ዘለግ ያለውን ጊዜ በማሳለፍ ሲጫወቱ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎዎች ደግሞ ረጃጅም ኳሶችን በማዘውተር መጫወት ይዘዋል።
ጨዋታው 19ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም የዩጋንዳው አጥቂ ስቴቨን ሙክዋላ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ወደ ግብ ልኮት ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ በጨዋታው የተገኘ ብቸኛ የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚ ነበረች። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመግባት የተወሰደባቸውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው ለማድረግ የጣሩት ኮንጎዎች ደግሞ በአብዛኛው መሐል ለመሐል ያተኮረ ጥቃት በመፈፀም መሪ ለመሆን መንቀሳቀስ ቀጥለዋል። አልፎ አልፎ ደግሞ በግራ መስመር በተሰለፈው ምፒያ ንዜንጌሊ ማክሲ በኩል ጥቃቶችን ለመፈፀም ሞክረዋል። ይህ ቢሆንም ግን የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ጠንከር ብለው ወደ ሜዳ የገቡ የሚመስሉት ኮንጎዎች በ52ኛው ደቂቃ ካብዊ ዋ ባንቱ ቤንጃሚም ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመታው ኳስ የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝረዋል። ዩጋንዳዎችም የተጫዋች ለውጥ በማድረግ በመጀመሪያው አጋማሽ ስኬታማ ያልነበረውን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማስተካከል ሞክረዋል። በተለይ ሳሊም አብደላህ ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በማድረሱ ረገድ ጥሩ ሆኖ ታይቷል። ነገርን የግብ ዘቡን ኢፎንግ ሊዮንጎን ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
👉ጂቡቲ 0-3 ኬንያ
ገና ከጅማሮው ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጊዜ መሪ ለማግኘት ተቃርቦ ነበር። በዚህም በ5ኛው ደቂቃ ካሊድ ኦስማን ዓሊ የኬንያ ተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ኬንያዎች በበኩላቸው በ11ኛው ደቂቃ በጨዋታው ባደረጉት የመጀመሪያ ሙከራ ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ጁጉና ኮሊንስ በግራ መስመር ያገኘውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ ጂቡቲዎች መረብ ላይ አሳርፎታል።
ግቡ ካስተናገዱ በኋላም ሳይደናገጡ ኳሱን በማንሸራሸር ጨዋታውን የቀጠሉት ጂቡቲዎች በ38ኛው ደቂቃ ሳብሪ ዓሊ መሐመድ አክርሮ ከሳጥን ውጪ በመታው ኳስ አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። ነገርግን ተጫዋቹ የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪም ቡድኑ የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨመሩት ሁለት ደቂቃዎች መሐል ላይም ጥሩ ጥቃት የፈፀመ ቢሆንም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ሳይችል ቀርቷል። በዚህም አጋማሹ በኬንያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አንድ ለምንም መሪነት ተገባዷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ ተጠናክረው የመጡት ኬንያዎች በአጋማሹ የመጀመሪያ ደቂቃዎች መሪነታቸውን ለማስፋት ተንቀሳቅሰዋል። በተለይ አቶላ ሄነሪ በ50ኛው ደቂቃ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረበት አጋጣሚ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል የማግኛ ምርጥ ዕድል ነበረች። አሁንም ጂቡቲ የግብ ክልል ለመድረስ ያልቦዘኑት ኬንያዎች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ፍሬ አፍርቶ በ63ኛው ደቂቃ ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ኦቲኖ ሬጋን ወደ ቀኝ ባዘነበለ ቦታ ያገኘውን ኳስ የግብ ዘቡ ነስረዲን አፕቲዶን ጀርባ የሚገኘው መረብ ላይ አሳርፎታል።
እንደ መጀመሪያው አጋማሽ እርጋታ የተሞላበት አጨዋወት መከተል የተሳናቸው ጂቡቲዎች ተከታታይ የተጫዋች ለውጥ አድርገው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ይባስ ብሎም መደበኛው ጨዋታ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀሩት ኦሉች ኦቺንግ በግንባሩ ባስቆጠረባቸው ጎል በምድቡ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል ለተጋጣሚ አስረክበው ወጥተዋል።
በትናንትናው ዕለት በደማቅ ሁኔታ የተጀመረው የሴካፋ ውድድር በነገው ዕለት ጨዋታዎች አይደረጉበትም። ከነገ በስተያ ከእረፍት መልስም በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ቡሩንዲ እና ኤርትራ 10:00 ሲል የምድብ ሁለተኛ ጨዋታቸውን በማድረግ ውድድሩ የሚቀጥል ይሆናል።