ባለፈው ሳምንት ለሀድያ ሆሳዕና ፈርሞ የነበረው ስንታየው መንግሥቱ ወደ ወላይታ ድቻ ተመልሷል።
በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም እየተመሩ ለቀጣዩ የውድድር ዓመት ተጫዋቾችን ማስፈረም ዘግይተው የጀመሩት የጦና ንቦቹ በቅርቡ ከተጫዋች ውል ማራዘም እና አዳዲስ ተጫዋቾችን ከማስፈረም አንፃር እየታየባቸው ባለው ደካማነት በርካታ የክለቡ ደጋፊዎች በክለቡ አመራሮች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞን ሲያሰሙ በቅርቡ መመልከት ችለናል፡፡
የክለቡ ደጋፊዎች ከተቃወሙበት አንዱ የሆነው ስንታየው መንግሥቱ ለሀድያ ሆሳዕና የመፈረሙ ጉዳይ ነበር። ይሄንንም ተከትሎ ወደ ሀድያ ሆሳዕና በማምራት የሁለት ዓመት ውል ፈርሞ የነበረው አጥቂው ስንታየው መንግሥቱ በሀድያ ሆሳዕና የፈረመው ውል ባለመፅደቁ ሁለተኛ ፊርማውን ለወላይታ ድቻ በከፍተኛ ገንዘብ በዛሬው ዕለት ፈርሞ በድጋሚ በይፋ የጦና ንቦቹን መቀላቀሉ ታውቋል።
በሌላ ዜና ክለቡ ከሰሞኑ ውላቸውን ለማራዘም ተስማምቶ የነበረውን የያሬድ ዳዊት፣ መልካሙ ቦጋለ፣ አናጋው ባደግ እና አንተነህ ጉግሳን ውልም ከስንታየው በተጨማሪ ለሁለት ዓመት ማራዘሙን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ሳሙኤል ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡