በድንገት ህይወቱ ያለፈውን ዳኛ የሚዘክር ውድድር ተካሄደ

በአዲስ አበባ እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፌደራል ዳኝነት እያገለገለ የነበረውና በድንገት ህይወቱ ያለፈው ተስፈኛ ወጣት ዳኛ ጌዲዮን ሄኖክን የሚያስታውስ ውድድር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ተካሂዷል።

አጭር በሆነው የዳኝነት ህይወቱ ብዙዎች ዘንድ እድገቱን እየጠበቀ ከሄደ ወደፊት ተስፋ ከሚጣልባቸው ዳኞች መካከል አንዱ እንደሚሆን የተነገረለት ፌደራል ረዳት ዳኛ ጌዲዮን ሄኖክ ባሳለፍነው ዓመት ልክ የዛሬዋ ቀን ሐምሌ 16 ነበር በድንገተኛ አደጋ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ያለፈው።

ታዲያ የሙያ ባልደረቦቹ እና አስቀድሞ በመምህርነት ሙያ የሚያስተምርባቸው የዐፄ ልብነ ድንግል እና የቀጨኔ ደብረ ሰላም ት/ቤት መምራህኖች እንዲሁም በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚገኙ መምራህን ማህበራት በጋራ በመሆን ያዘጋጁት የመታሰቢያ ውድድር ረፋድ አምስት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ተካሂዷል።

ትልቅ አላማ ባነገበው በዚህ ውድድር በጨዋታው ከተመዘገበው ውጤት ባሻገር ጌዲዮንን ለማስታወስ የእርሱ ምስል ያረፈበትን ቲሸርት በመልበስ እና የህሊና ፀሎት በማድረግ አስበውት ውለዋል። በተጨማሪም ብቸኛ ልጃቸው ለሆነው ወላጅ እናቱ ይሆን ዘንድ ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ አድርገዋል።