በቀድሞ አሠልጣኛቸው አቤቱታ የቀረበባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
አሠልጣኝ ፍስሀ ጥዑመልሳን በመጋቢት ወር ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፃፉት አቤቱታ ” ከመስከረም 1 ቀን 2013 እስከ ነሐሴ 30 ቀን 2013 ውል እያለኝ አግባብ በሌለው በዲስኘሊን ምክንያት ውሌ እንደተቋረጠ ከክለቡ ተነግሮኛል። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ የቀሪ የ7 ወር ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም እንዲያሰጠኝ” ሲሉ ጠይቀው ነበር። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ በአሠልጣኙ እና በክለቡ በኩል የቀረቡትን ዝርዝር መከራከሪያዎች በጥልቀት ከተመለከተ በኋላም በዛሬው ዕለት ክለቡ ላይ ወሳኔ መስጠቱ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በዚህም ኮሚቴው አሠልጣኙ ስህተቱን እንዲያርም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ሊያርም ባለመቻሉ ከሥራ ተሰናብቷል በማለት ክለቡ ያቀረበው ምክንያት ተገቢው ሆኖ አልተገኘም ብሏል። ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ከስህተት አልታረምክም ብሎም የሥራ ውል ማቋረጥ ፍትሀዊ እንዳልሆነ በውሳኔው የገለፀው የዲሲፕሊን ኮሚቴው አሠልጣኙ እና ክለቡ በውላቸው አንቀጽ 5 መሠረት በግልግል የመፍታት መብታቸው እንደተጠበቀ መሆኑን አስታውሶ ክለቡ አሠልጣኙን ወደ ሥራ እንዲመልስው በውሉ ጊዜ ያልተከፈለው ደመወዝ እንዲከፍለው ወስኗል። ክለቡም ውሳኔ በደረሰው በ7 ቀናት ውሰጥ የተወሰነውን ውሳኔ እንዲፈፅም የማይፈጽም ከሆነ ከማንኛውም ውድድር እንዲታገድ እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ሲወሰን ይግባኝ ግን መብት እንደሆነ ተጠቁሟል።
ዲሲፕሊን ኮሚቴ ያስተላለፈው ሙሉ የውሳኔ ደብዳቤ ከስር ተቀምጧል 👇