ጅቡቲን የረታችው ደቡብ ሱዳን በምርጥ ሁለተኝነት እንዲሁም ከዩጋንዳ ጋር ነጥብ የተጋራችው ታንዛኒያ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል።
👉ጅቡቲ 0-2 ደቡብ ሱዳን
ከጂቡቲዎች በተሻለ ኳሱን ተቆጣጥረው መጫወት የቻሉት ደቡብ ሱዳኖች በ8ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት እጅግ ተቃርበው ነበር። በዚህ ደቂቃም ዳኒ ሉዋል ጉማኖክ ከወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ያገኘውን ኳስ በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ዳድቶ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ይሄንን ሙከራ ያደረገው ዳኒ ጉማኖክ ከ8 ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ ሌላ የሰላ ጥቃት ፈፅሞ ነበር። በዚህም ተጫዋቹ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ የላከው ኳስ በተመሳሳይ መዳረሻው የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወደ ውጪ መውጣት ሆኗል።
ጫና የበዛባቸው ጂቡቲዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በማፈግፈግ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ብቻ በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። አልፎ አልፎም ከቆመ ኳስ ተጋጣሚን ለመፈተን ጥረዋል። በዚህ እንቅስቃሴም ኦማር ሙሐመድ መሐሙድ የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ጥሩ ቅጣት ምት ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረም ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ደቡብ ሱዳኖች በ48ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት ስቴፈን ፓዋር ሎኒ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ነስረዲን አብዲ አፕቲዶን አድኖታል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ናቢል ነስረዲን አህመድ በግንባሩ ሲገጨው በድጋሜ ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል።
በዚህኛውም አጋማሽ ግብ ላለማስተናገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ጂቡቲዎች አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው ቀጥሏል። ደቡብ ሱዳኖች ግን ወደ ቀጣይ ዙር የሚያሳልፋቸውን ነጥብ ለማግኘት መታተር ቀጥለዋል። በዚህም በ77ኛው ደቂቃ ላይ ስቴፈን ሎኒ ከጥሩ ቦታ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ለጥቂት ሲመለስበት ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ የገባው አብደላህ አሳድ ሙሳ ሌላ ሙከራ ከሳጥን ውጪ ሰንዝሮ ዒላማውን ስቶበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ሎኪ ኢማኑኤል ፒተር በተከላካዮች መሐል የደረሰውን ተንጠልጣይ ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ የዕለቱ አራተኛ ዳኛ ጭማሪ ደቂቃውን ሲያሳዩ በጨዋታው ሦስት ነጥብ ማግኘት እጅግ የሚገባት ደቡብ ሱዳን የልፋቷን ፍሬ አግኝታለች። በዚህም አሉክ አቢዮር ጥሩ ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ የቡድኑን ጭንቀት ጋብ አድርጓል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሎኪ ኢማኑኤል ፒተር ላይ የተሰራውን ጣፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ዶምኒክ ኮርኒሊዮ ወደ ግብነት ቀይሮ ደቡብ ሱዳኖች ጨዋታውን ሁለት ለምንም እንዲያሸንፉ ሆኗል።
ውጤቱን ተከትሎ ደቡብ ሱዳን ነጥቧን ሦስት በማድረስ የውድድሩ ምርጥ ሁለተኛ ሆና ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅላለች።
👉ዩጋንዳ 1-1 ታንዛኒያ
ጥሩ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ የሰላ ሙከራ ማስተናገድ የጀመረው ከ7ኛው ደቂቃ ጀምሮ ነው። በተጠቀሰው ደቂቃም የታንዛኒያው ተጫዋች ጆሴፍ ምኬሌ ከመዓዘን የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ሞክሮት የግብ ዘቡ አውጥቶበታል።
በአንፃራዊነት ሻል ብለው የታዩት ዩጋንዳዎች በ13ኛው ደቂቃ ስቴቨን ሙክዋላ ከቀኝ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ በመላኩ መሪ ሊሆኑ ነበር። ከደቂቃ በኋላም ቡድኑ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ተሰርቶበት የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኝም ስቴቨን ሙክዋላ ሳይጠቀምበት ዕድሉን አምክኖታል። አሁንም ታንዛኒያ የግብ ክልል መድረስ ያላቆሙት ዩጋንዳዎች በ19ው ደቂቃ አብዱል ካሪም ዋታምባላ ሌላ ሙከራ ሰንዝሮ አልቀመስ ያለው ሜታቻ ቦኒፌስ ምናታ መልሶባቸዋል።
ጨዋታው ቀጥሎም ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ ግብ ለማስቆጠር ወደ ዩጋንዳ የግብ ክልል ያመሩት ታንዛኒያዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው መሪ ሆነዋል። በዚህም በ32ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሶስ ፒተር ባጃና ጎል አድርጎታል። ግብ ካስተናገዱ በኋላም ሳይደናገጡ መጫወት የቀጠሉት ዩጋንዳዎች ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ አቻ የሆኑበትን ጎል ቀድሞ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ባመከነው ስቴቨን ሙክዋላ አማካኝነት አስቆጥረዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም አንድ አቻ ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በዝናባማው የአየር ሁኔታ የተጀመረው የጨዋታው የሁለተኛ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ እንደ አየር ንብረቱ ቀዝቃዛ ፉክክር ተስተውሎበታል። ቡድኖቹም ረጃጅም ኳሶችን በማዘውተር ሲጫወቱ ታይቷል። በአንፃራዊነት ግን ሻል ማለታቸውን የቀጠሉት ዩጋንዳዎች በፈጣኑ አጥቂያቸው ስቴቨን ሙክዋላ አማካኝነት ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ የሚያስችላቸውን ነጥብ ለማግኘት ታትረዋል።
ሦስት ነጥብ ካላገኙ ከምድቡ መውደቃቸውን የሚያረጋግጡት የወቅቱ የሴካፋ አሸናፊ ዩጋንዳዎች የተጫዋች ለውጦችን አከታትሎ በማስገባት ግብ ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረውም ተቀይሮ የገባው ሀኪም ኪዋኑካ ከመዓዘን የተሻገረለትን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ ግብ ጠባቂው ይዞበታል። ቡድኑ ልፋቱን እስከ መጨረሻው ቢቀጥልም ውጥኑሳይሰምር ጨዋታው አንድ አቻ ተጠናቋል።
ነጥቧን አራት ያደረሰችው ታንዛኒያ የምድቡ የበላይ ሆና ግማሽ ፍፃሜውን ስትቀላቀል ዩጋንዳዎች ግን በሁለት ነጥብ ከምድቡ ወዳቂ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የጂቡቲ እና የደቡብ ሱዳንን አቻ መውጣት እንዲሁም የታንዛኒያን ማሸነፍ አልያም በጠባብ ጎል አቻ መውጣት ሲጠብቅ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግማሽ ፍፃሜውን ለመቀላቀል የነበረው ተስፋ ሙሉ ለሙሉ ጨልሟል።