ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የአውስትራሊያ እና የስፔን ጨዋታን በዋና ዳኝነት ዕሁድ አመሻሽ ይመራል፡፡
በኮቪድ 19 ምክንያት በአንድ ዓመት ተራዝሞ በይፋ በትናንትናው ዕለት በመክፈቻ መርሐግብር የተጀመረው የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ የእግር ውድድሮች በሁለቱም ፆታ ቀደም ብሎ ከቀናት በፊት የተጀመረ ሲሆን የምድብ ማጣሪያዎችም ቀጥለዋል፡፡ ከቀናት በፊት ሜክሲኮ ከ ፈረንሳይ ያደረጉት ጨዋታ ላይ በአራተኛ ዳኝነት አገልግሎ የነበረው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ ነገ አመሻሽ 12፡30 በምድብ 3 ግብፅ፣ አርጀንቲና፣ አውስትራሊያ እና ስፔን በሚገኙበት ምድብ ውስጥ አውስትራሊያ እና ስፔን የሚያከናውኑትን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት የመጀመሪያ የኦሊምፒክ ጨዋታውን እንዲመራ ተመርጧል፡፡
ኬኒያዊው ጊልቨርት ቼሮይት እና ደቡብ ሱዳናዊው መሐመድ ኢብራሂም የበአምላክ ረዳቶች ሲሆኑ ጃፓናዊው ሄሮይኪ ኪሙራ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት በጋራ ይመሩታል፡፡ ሦስት ተጨማሪ ዳኞች በበኩላቸው በVAR ዳኝነት በጋራ ሆነው እንደሚያጫውቱ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡