ከአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጋር የተለያየው ሰበታ ከተማ ከደቂቃዎች በፊት አዲስ አሠልጣኝ አግኝቷል።
በተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ37 ነጥቦች አምስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሰበታ ከተማ አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን በባህር ዳር ከተማ ከተነጠቀ በኋላ አዲስ አሠልጣኝ ለመሾም የቅጥር ማስታወቂያ በማውጣት እንቅስቃሴ ጀምሮ እንደነበረ ይታወቃል። ከአስር በላይ አሰልጣኞች የቅጥር ማስታወቂያውን በማየት የስራ ልምዳቸውን ቢያስገቡም የክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ በመጨረሻም በሁሉም ረገድ የወጣውን መስፈር ያሟላሉ በማለት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን በሦስት ዓመት ውል መሾሙ ተረጋግጧል።
የቀድሞ ደቡብ ፖሊስ፣ ደደቢት፣ አዳማ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወልዲያ እና መከላከያ አሠልጣኝ የነበሩት ዘላለም በዘንድሮ የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ወደ ወላይታ ዲቻ በማምራት ላለመውረድ ሲፍጨረጨር የነበረውን ክለብ በጥሩ መነሳሳት እንዲተርፍ አድርገውት ነበር። በ2008 ክረምት ወራት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሠልጣኝ (የገብረመድህን ኃይሌ ምክትል) በመሆን ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን የመሩት አሠልጣኙ በቀጣይ ከሰበታ ከተማ ጋር የአሠልጣኝ ህይወታቸውን ለመቀጠል ፊርማ አኑረዋል።