ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ተሳታፊ የሚያደርገው የሴካፋ ዞን የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ጨዋታዎች መቼ እንደሚጀምሩ ታውቋል።
በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚደረገው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ለመሳተፍ በአህጉሪቱ የሚገኙ ሀገራት የሊግ አሸናፊዎች በስድስት ዞን በተከፋፈሉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ ውድድሩ የሚወስዳቸውን ትኬት የሚቆርጡ ይሆናል። የ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በውድድሩ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ አዳዲስ ተጫዋቾችን አካቶ ዝግጅቱን ከጀመረ ሰነባብቷል።
ቀድሞ ከሐምሌ 10 ጀምሮ እንደሚደረግ ተነግሮ የነበረው ውድድሩ ላልተገለፀ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጎ እንደነበር አይዘነጋም። አሁን በተሰማ መረጃ ደግሞ ከውድድሩ አስተናጋጅ ሀገር ኬንያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ከካፍ ጋር በተደረገ ንግግር የቀጠናው ውድድር ከነሃሴ 1 ጀምሮ እስከ 15 ድረስ እንዲደረግ መወሰኑን የሚጠቁም ነው። ውድድሩም በስምንት የቀጠናው ክለቦች መካከል በናይሮቢ የሚደረግ ሲሆን የውድድሩ አሸናፊ በቀጣይ ዓመት በግብፅ አስተናጋጅነት በሚካሄደው አህጉራዊ የክለቦች ውድድር ላይ ተሳታፊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል።