የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ-ግብር የሆነው የዩጋንዳ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጨዋታ ዩጋንዳን አንድ ለምንም አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።
በረጃጅም ኳሶች፣ ፈጣን ሽግግሮች እና ጉሽሚያዎች ታጅቦ መደረግ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጅማሮ እርጋታ የተሞላበት አልነበረም። ቡድኖቹም ቶሎ ቶሎ ኳስ እየተነጣጠቁ ሀይል የበዛበት እንቅስቃሴ ሲከተሉ ታይቷል። ጨዋታው 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ዩጋንዳዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ሰንዝረዋል። በዚህም ሙሳ ራማዳን ከወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ላይ የተገኘው የቅጣት ምት ሲሻማ አግኝቶ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ቢጥርም ሀሳቡ ሳይሰምር ቀርቷል።
በአንፃራዊነት በተሻለ የውድድሩ ተጋባዥ ሀገር የግብ ክልል መድረስ የቀጠሉት ዩጋንዳዎች በ28 ደቂቃ ስቴቨን ሰርዋዳ አክርሮ በመታው ነገርግን የግብ ዘቡ ኢፎንጊ ሊዮንጎ ብሩዴል በተቆጣጠረው ኳስ ግብ ሊያገኙ ነበር። በ37ኛው ደቂቃ ደግሞ ሌላ የቅጣት ምት ያገኘው ቡድኑ በሳሙኤል ሴንዮንጆ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ዳድቶ ነበር። ነገርግን ተጫዋቹ የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ግን የተሻሉ የነበሩት ዩጋናዳዎች ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም ናጂብ ይጋ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታውም በዩጋንዳ አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ለመመለስ እጅግ መታተር የጀመሩት ኮንጎዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ለውጦ በማስገባት ግብ ፍለጋቸውን ተያይዘውታል። ነገርግን ዩጋንዳዎች አልቀመስ ብለው ጨዋታው ቀጥሏል። በ60ኛው ደቂቃ ግን ቡድኑ ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። በዚህ ደቂቃም ስቴቨን ሙክዋላ በፈጣን ሽግግር ተጋጣሚ ክልል ደርሶ ወደ መሐል ያሻገረውን ኳስ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተከላካይ ራሱ ላይ ሊያስቆጥረው ነበር። ነገርግን ኳሱን ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶታል።
የአቻነት ጎል ለማግኘት እጅግ የፈለጉት ኮንጎዎች በ64ኛው ደቂቃ ውጥናቸው ፍሬ ሊያፈራ ከጫፍ ደርሶ ነበር። በዚህም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኢካንጋ ጆናታን ያሻገረውን ኳስ ባሌኬ ኦቶስ ያን በግንባሩ ወደ ግብነት ሊቀይረው የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ዒላማውን የጠበቀውን ኳስ ተቆጣጥሮታል። ዩጋንዳዎች ደግሞ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት በሰከንዶች ልዩነት ሁለት ተከታታይ ሙከራዎችን በማድረግ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት የፈለጉ መስለዋል። ኮንጎዎችም እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ድል የተቀዳጀችው ዩጋንዳ በውድድሩ አምስተኛ ደረጃን ለመያዝ ከኤርትራ ጋር ከነገ በስትያ ጨዋታ የምታደርግ ይሆናል። በጨዋታው እጅ የሰጠችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ሰባተኛ ደረጃን ለመያዝ የኢትዮጵያ አቻዋን የምትፋለም ይሆናል።