በዝውውር ገበያው እየተሳተፈ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል፡፡
ሀዋሳ ከተማን በድምሩ ለአራት ዓመታት በግብ ጠባቂነት ያገለገለው ቶጓዊው ሶሆሆ ሜንሳ ከክለቡ ጋር በመለያየቱ ጋናዊው ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ በአንድ ዓመት ውል በቦታው ተተክቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ለሀገሩ ክለቦች ሚዴአማ፣ አሻንቲ ኮቶኮ እንዲሁም ለዛምቢያው ሉሳካ ዳይናሞስ የተጫወተው እና ለጋና ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም ከዚህ ቀደም መጫወት የቻለው ሙንታሪ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኃላ ለጅማ አባ ጅፋር በመጫወት ከሀገራችን እግር ኳስ ጋር የተዋወቀ ሲሆን የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ደግሞ በሀዲያ ሆሳዕና ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ ቆይቶ ሀዋሳ ከተማን ለማገልገል አምርቷል፡፡
የተከላካይ አማካዩ ኤርሚያስ በላይ የልጅነት ክለቡ ሀዋሳ ከተማን ተቀላቅሏል፡፡ እግር ኳስን በሀዋሳ ከተማ የተስፋ ቡድን የጀመረው እና ወደ ዋናው ቡድን የማደግ ዕድልን ከዚህ ቀደም ያገኘው ኤርሚያስ በሰበታ ከተማ፣ ደቡብ ፖሊስ እና የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት እስከ አጋማሹ በከፍተኛ ሊጉ ኢኮሥኮ እና አርባ ምንጭ ከተማ ሲጫወት ቆይቷል፡፡ ቁመተ ረጅሙ የመሐል ሜዳ ተጫዋች በተለይ ከዚህ ቀደም መጫወት ወደቻለበት አርባምንጭ ከተማ ያለፉትን ስድስት ወራት በመጫወት ክለቡንም ወደ ፕሪምየር ሊጉ በማሳደግ በአዞዎቹ ቆይታን ካደረገ በኃላ ወደ ልጅነት ክለቡ ሀዋሳ በመመለስ ፊርማውን የሁለት ዓመት ፊርማውን አኑሯል፡፡
ሌላኛው አዲስ ፈራሚ አብዱልባሲጥ ከማል ነው፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ የ2013 የውድድር አመትን ስሑል ሽረን ከለቀቀ በኃላ በሰበታ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን ቡድኑን የለቀቀው ጋብሬል አህመድን ቦታ ይሸፍናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በንቃት ዝውውሩ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ፀጋሰው ድማሙ እና በቃሉ ገነነን ቀደም ብሎ ያስፈረመ ሲሆን በድምሩ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን እስከ አሁን ወደ ስብስቡ አካቷል።