የ2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና የከፍተኛ ሊግ የዝውውር መከፈቻ ቀን መቼ እንደሆነ ይፋ ተደርጓል።
የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የዝውውር መስኮት ከሐምሌ ወር መጀመሪያ አንስቶ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከፕሪምየር ሊጉ ባሻገር የሚደረጉት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ እና የከፍተኛ ሊግ የዝውውር መስኮት እስከ አሁን ሳይከፈቱ የሰነበቱ ሲሆን በዛሬው ዕለት ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለክለቦች በላከው ደብዳቤ ዝውውሩ የሚከፈትበትን ቀን ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን እንዲሁም ደግሞ የከፍተኛ ሊግ ውድድር የዝውውር ቀናት ከነሐሴ 10 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 10 ድረስ እንዲደረግ ፌዴሬሽኑ ለክለቦች ማሳወቁን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ተሳታፊ የሆኑ አንዳንድ ክለቦች ቀደም ብለው ተጫዋቾችን እያስፈረሙ የሚገኝ ሲሆን አብዛኛዎቹ ዝውውራቸውን በክልሎቻቸው ባሉ ፌዴሬሽኖች እያፀደቁ ይገኛል፡፡
በተያያዘ መረጃ የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የዝውውር መስኮቱ የሚከፈትበት ቀን እስካሁን ያልተገለፀ ሲሆን እንደ ምክንያትነት ላለመከፈቱም የክልል ክለቦች ሻምፒዮና በሀዋሳ እየተደረገ በመሆኑ እና እስካሁን ባለመጠናቀቁ የተነሳ እንደሆነም ሰምተናል፡፡