ከሳምንታት በፊት አብርሃም መብራቱን አሠልጣኝ አድርጎ መሾሙ የተገለፀው ባህር ዳር ከተማ በይፋ ከአሠልጣኙ ጋር ተፈራርሟል።
ይጀመራል ተብሎ ከተነገረው አንድ ሰዓት ዘግይቶ መካሄድ የጀመረው የፊርማ ሥነ-ስርዓቱ እና ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፣ የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብርሃም አሰፋ፣ የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ልዑል እንዲሁም አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ እና አቶ ጋሻው አበዛ ተገኝተዋል። በቅድሚያም የክለቡ ፕሬዝዳንት ድረስ ሳሕሉ (ዶ/ር) እና አሠልጣኝ አብርሃም የፊርማ ሥነ-ስርዓት አከናውነዋል። ክለቡ ከአሠልጣኙ ጋር ውል ከመያዙ በተጨማሪ አደረጃጀቱን ለማዘመን እና ተቋማዊ አቋሙን የበለጠ ለማደራጀት ከአቶ ጋሻው አበዛ (ተመራማሪ) ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።
የፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ከተከናወነ በኋላ የክለቡ ምክትል ፕሬዝዳንት ባለፉት ሁለት ዓመታት ቦርዱ በአዲስ መልክ ከተቋቋመ በኋላ ጽሕፈት ቤት በተደራጀ መልኩ ከመክፈት ጀምሮ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎችን ሲሰሩ እንደነበረ አመላክተዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ንግግራቸውን ቀጥለውም “ክለቡ በሜዳ ላይ ውጤታማ እንዲሆን ከመንቀሳቀሳችን በተጨማሪ ተቋማዊ አደረጃጀቱን እና መዋቅሩን ለማዘመን ልምድ እና ዕውቀት ያላቸውን ሰዎችን ስንፈልግ ነበር። አሁን ደግሞ ፍላጎት እና መልካም ፍቃደኝነት ካሳዩት አቶ ጋሻው ጋር ለመስራት ተስማምተናል።” ብለው ከአሠልጣኙ ውጪ የተፈፀመውን ስምምነት አብራርተዋል።
አቶ አብርሃም በንግግራቸው ማብቂያ ላይ ክለቡ ከመንግስት ጥገኝነት ወጥቶ ራሱን እንዲችል የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመላክተው በአጭር ጊዜ ከመንግስት ከሚያገኘውን ድጋፍ (ከ40-40%) ወጥቶ አመታዊ በጀቱን እና ወጪውን እንዲችል እንቅስቃሴ ላይ መኮኑን እና የካምፕ እና የገቢ ማመንጫ ህንፃ ለመገንባት 17 ሺ ካሬ ቦታ እንደተረከቡ አስረድተዋል።
ከምክትል ፕሬዝዳንቱ ንግግር በኋላ አዲሱ የክለቡ አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ መድረኩን ተቀብለው ንግግር ማድረግ ጀምረዋል። አሠልጣኙም ከክልሉ ከንቲባ ጀምሮ ያሉት የክለቡ አመራሮች ለስፖርቱ የሰጡትን ትኩረት አድንቀው የአካባቢውም ባለ ሀብቶች ለእግርኳሱ ያሳዩትን ድጋፍ አበረታተዋል።
“በክልሉ የሚገኙት ባለሀብቶች ለእግርኳሱ የሚያደርጉት ድጋፍ እና ከከንቲባ ጀምሮ ክለቡን የሚመሩት አመራሮች ለባለሙያዎች ያላቸውን ቀረቤታ የሚደነቅ ነው። ከዚህ ድጋፍ ጀርባ መስራት ጥሩ ስለሆነም ክለቡን ለመያዝ ወስኛለሁ። ከዚህ በተጨማሪም ሊያድግ የሚችል እና ሊያሰራኝ የሚችል ከባቢ ያለው ክለብ በመሆኑ መዳረሺያ አድርጌዋለሁ። ከምንም በላይ ደግሞ በ2 ዓመት የብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ሲደግፈኝ እና ሲያበረታታኝ የነበረው ማኅበረሰብ ጋር አብሬ ለመስራት ስለሚያስችለኝ ክለቡን መርጬዋለሁ። ያኔ ብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ ካልነበረበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አይቮሪኮስቱ ጨዋታ ድረስ የአካባቢው የስፖርት ቤተሰብ ከጎኔ አብሮኝ ስለነበር ያ ፍቅር እንደሚቀጥል በመተማመኔ ነው ክለቡ የመጣሁት።” ብለዋል።
የሁለት ዓመት ውል የፈረሙት አሠልጣኝ አብርሃም በዚህ ዓመት ክለቡን ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ እና አስተማማኝ ቡድን ለመገንባት መታሰቡን ገልፀዋል። በቀጣይ ዓመት ደግሞ ይህ አስተማማኝ ቡድን እስከ ሻምፒዮናነት እንዲደርስ ሥራዎች እንደሚሰሩ አመላክተዋል። አሠልጣኙ በማብራሪያቸው አስከትለው ቡድኑን ከያዙት በኋላ የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት አያይዘው ተናግረዋል።
“እንዳልኩት ቡድኑን የመገንባት እና ተፎካካሪ የማድረግ ሥራ ይጠበቅብኛል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በክልሉ የሚገኙ አሠልጣኞችን የማብቃት እና የማገዝ ሥራ ይሰራል። ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ ታዳጊዎችን የማፍራት እንዲሁም ለክለቡ፣ ለክልሉ አልፎም ለሀገር የሚጠቅሙ ወጣቶችን የማፍራት ተግባር ይከናወናል። በመጨረሻም ደግሞ የተጀመረውን ክለቡን ዘመናዊ የማድረግ ሥራን በአቅሜ የማግዝ ይሆናል።”
ከአሠልጣኙ በኋላ የክለቡን መዋቅር ለማዘመን ስምምነት የፈፀሙት ጋሻው አበዛ (ዶ/ር) የክለቦችን አወቃቀር ለማዘመን የሚሰራውን ሥራ በአጭሩ አብራርተዋል።
” ክለቦችን ከማዘመን ባሻገር ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ሰፊ ጥናት እየተከናወነ ነው። ከፋሲል ከነማም ጋር በዚህ መልኩ ይቀጥላል። የባለቤትነት ይዞታቸው በሁሉም አካላት (ከመንግሥት፣ ከድርጅቶች፣ ከግለሰቦች ጋር) ሼር ይደረጋል። ይህ ከመሆኑ በፊት ግን የክለቡን አሠራር ማዘመን አለብን። ስፖንሰር ሺፕ ከልግስና አልፎ ወደ ቢዝነስ ሀሳብ እንዲሸጋገር መሥራት፣ የደጋፊዎች ዲጂታል ምዝገባ ማካሄድ፣ የቁሳቁስ ሽያጮች ሥርዓት መዘርጋት፣ ክለቡ ከእግርኳስ ውጪ ሌሎች ሥራዎችን የሚሠራበት መንገድ መቀየስ የምንራቸው ተግባራት ናቸው።” ብለዋል።
የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ እና የክለቡ ፕሬዝዳንት ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) አሠልጣኝ አብርሃም ልምድ እና ዕውቀት ያለው ስለሆነ እንደመረጡት እና ክለቡ ከዘንድሮ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ በማሰብ እንደተሾመ ጠቁመዋል። ከከንቲባው የማጠቃለያ ንግግር በፊት ደግሞ አሠልጣኝ አብርሃም የቀድሞ አንጋፋ እና ባለ ታሪክ ተጫዋቾችን በምክትልነት ለማምጣት ያቀረቡት ጥያቄ በቦርዱ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን ገልፀው አዳነ ግርማን ለማምጣት ንግግር መጀመራቸውን አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የምልመላ ቡድን (scouting group) እና የቴክኒክ ጥናት ቡድን (TSG) ቡድንም እንደሚቋቋም አብራርተዋል። በዋነኝነት ደግሞ በክልሉ ያሉ የቀድሞ ተጫዋቾችን በሚቋቋሙት የቴክኒክ ክፍሎች ለማካተት ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። በአሁን ግን የሥነ-ምግብ እና የስፖርት ካይኮሎጂ ባለሙያ ለማምጣት ንግግር ላይ መኮኑንም ገልፀዋል።