በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆኑን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ድልድሉን በቀጣይ ሳምንት ያውቃል።
ከወራት በፊት በቀጣይ ዓመት በሚደረገው የአህጉሩ ትልቁ የእግርኳስ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሀገራት በቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተለይተው መታወቃቸው ይታወሳል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በምድብ 11 ከአይቮሪኮስት፣ ማዳጋስካር እና ኒጀር ጋር ተደልድሎ የምድቡ 2ኛ ሆኖ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ከስምንት ዓመታት በኋላ አልፎ ነበር።
ካፍ አሁን እንዳስታወቀው ከሆነም በውድድሩ የሚሳተፉ 24 ሀገራት የምድብ ድልድላቸው በካሜሩን ያውንዴ ሴንተር በናይጄሪያዊቷ እውቅ አስተዋዋቂ እና ፕሮዲውሰር ሚሚ ፋዋዝ እና በካሜሩናዊው የቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ፕሮግራሞች አቅራቢ በሆነው ሊዮናርድ ቻተሌን በሚመራው የማክሰኞ ምሽት መርሐ-ግብር የሚያውቁ መሆኑን አመላክቷል።
24ቱ ሀገራት በፊፋ ባላቸው ደረጃ መሠረት በአራት ቋቶች ውስጥ መቀመታቸው ሲገለፅ ኢትዮጵያም በቋት አራት ከማላዊ፣ ሱዳን፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኮሞሮስ እና ጋምቢያ ጋር ተቀምጣለች። በቋት አንድ የውድድሩ አስተናጋጅ ካሜሩን እና የወቅቱን የውድድሩ አሸናፊ አልጄሪያን ጨምሮ ሴኔጋል፣ ቱኒዚያ፣ ሞሮኮ እና ናይጄሪያ አብረው ሲሆኑ በቋት ሁለት ደግሞ ግብፅ፣ ጋና፣ አይቮሪኮስት፣ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ጊኒ ተቀምጠዋል። ቋት ሦስት ላይ ደግሞ ኬፕቨርዲ፣ ጋቦን፣ ሞሪታኒያ፣ ሴራሊዮን፣ ዚምባቡዌ እና ጊኒ ቢሳኦ ተደልድለዋል።
በአንድ ቋት ውስጥ የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖችም በዋናው ውድድር ላይ አብረው በአንድ ምድብ እንደማይገናኙ ተገልጿል። ምድቦቹም አራት አራት ቡድኖችን ያዘው ስድስት ቦታ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል። በ24 ሀገራት መካከል ሲደረግ ለሁለተኛ ጊዜ የሚሆነው ይህ አፍሪካ ዋንጫ ውድድርም ከጥር 1 – 29 (ጃኑዋሪ 9 – ፌብሩዋሪ 6) ድረስ ለመከወን ቀጠሮ ተይዞለታል።