በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሦስተኛ ጊዜ ለተራዘመው የሴካፋ ዞን የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት ዳግም ነገ ሲሰባሰብ ወደ ኬንያ የሚያመራበትም ቀን ታውቋል።
የወቅቱ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣይ ዓመት በሚደረገው የአፍሪካ ሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ እየተዘጋጀ ይገኛል። በግብፅ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ውድድር ላይ የሚሳተፉ ክለቦችም በስድስት ዞኖች ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚያደርጉ ሲሆን የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድርም ከነሐሴ 22 ጀምሮ በኬንያ አስተናጋጅነት የሚከወን ይሆናል።
በዚህ የማጣሪያ ውድድር ላይ የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ውድድሩ ለሦስተኛ ጊዜ ከመራዘሙ በፊት ዝግጅት ማድረግ በመጀመር ለ29 ቀናት ልምምድ የሰራ ቢሆንም ከሳምንታት በፊት የውድድሩ መጀመሪያ ቀን ከተገፋ በኋላ ለተጫዋቾቹ የሁለት ሳምንት ዕረፍት ሰጥቶ ነበር። ከሦስት ቀን በፊት የውድድሩ መጀመሪያ ቀን ነሐሴ 22 መሆኑ ሲገለፅ ደግሞ ክለቡ የመጨረሻ ምዕራፍ ዝግጅቱን ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ የነበረ ሲሆን በነገው ዕለትም ወደ ቢሾፍቱ በማቅናት ዝግጅቱን እንደሚቀጥል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
21 ተጫዋቾችን ይዞ እየተዘጋጀ የነበረው ክለቡ ነገ ከሰዓት በቢሾፍቱ ከተሰባሰበ በኋላ ከሰኞ ጀምሮ ልምምዱን እንደሚሰራ ታውቋል። ክለቡም ለተከታታይ አስር ቀናት ልምምዱን በስፍራው ከሰራ በኋላ ነሐሴ 20 ወደ ኬንያ ለመጓዝ ቀጠሮ ይዟል። ወደ ስፍራውም 21 ተጫዋቾች፣ አምስት የአሠልጣኝ ቡድን አባላት፣ አንድ የህክምና ባለሙያ እና የአስተዳደር ግለሰብ እንደሚያመሩ ተገልጿል።
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተመስርቶ የመጀመሪያ ጎል ያስቆጠረችው እና በአሁኑ ሰዓት በህክምና የስራ መስክ የተሰማራቸው ዶክተር እንደገና አዋሶ የክለቡ የህክምና ባለሙያ ሆና መቀጠሯ ተነግሯል።