የቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርን ለማስተናገድ ጥያቄ ያቀረበው የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ትናንት ግምገማ እንደተደረገለት ታውቋል።
የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአምስት ሳምንታት መርሐ-ግብሮችን (ከ5ኛ እስከ 10ኛ ሳምንት ድረስ) አስተናግዶ የነበረው የጅማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የቀጣይ ዓመት የሊጉን ውድድርንም ለማስተናገድ ዘግይቶም ቢሆን ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል። ከዚህ ቀደም የሀዋሳ እና አዳማ ዩኒቨርስቲ ስታዲየሞችን እንዲሁም የድሬዳዋ ስታዲየምን የገመገመው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርም ትናንት ወደ ጅማ በማምራት የስታዲየሙን አሁናዊ ሁኔታ እንደተመለከተ ለማወቅ ችለናል።
ከዋናው የመጫወቻ ስታዲየም ውጪ የልምምድ ሜዳዎች እና ሆቴሎች ላይም ምልከታ እንደተደረገ ተገልጿል። ወደ ስፍራው ያመራው ኮሚቴም ከዩኒቨርስቲው አመራሮች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉ እና መሻሻል አለባቸው የተባሉ ጉዳዮችን እንዳነሳ ሰምተናል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር በቀጣይ የባህር ዳር ስታዲየምን ለመመልከት ጉዞ እንደሚያደርግም ተጠቁሟል።