በቀጣይ ሳምንት ከሴራልዩን እና ዩጋንዳ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን በየትኛው ስታዲየም እንደሚያከናውን ተገልጿል።
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለኳታሩ የ2022 ዓለም ዋንጫ ለመብቃት ካለንበት ወር የመጨረሻ ቀናት ጀምሮ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ እንደሚጀምር ይታወቃል። ለምድቡ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታዎች (ከጋና እና ዚምባቡዌ) ዝግጅቱን አዳማ ላይ በመቀመጥ ሲያከናውን የሰነበተው ቡድኑም የፊታችን ሀሙስ እና እሁድ ከሴራሊዮን እና ዩጋንዳ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ያደርጋል።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ መሠረት ከሴራሊዮን እና ዩጋንዳ ጋር የሚደረጉት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ይከናወናሉ። ይህንን ተከትሎም በአሁኑ ሰዓት አዳማ የሚገኘው የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ስብስብም ከነገ በስትያ (ማክሰኞ) ወደ ባህር ዳር እንደሚያቀና ተጠቁሟል።
የመጀመሪያው የዋልያው ተጋጣሚ የሆነው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ነገ አዲስ አበባ እንደሚገባ ታውቋል። ብሔራዊ ቡድን ነገ አዲስ አበባ ደርሶ አዳሩን በመዲናው ካደረገ በኋላ በተመሳሳይ ማክሰኞ ጨዋታው ወደሚደረግበት ባህር ዳር እንደሚያቀና አረጋግጠናል።