ቻምፒዮንስ ሊግ ፡ ባህርዳር ለጨዋታው ተዘጋጅታለች

በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ 1ኛ ዙር ፍልሚያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ቲፒ ማዜምቤ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ በመጪው እሁድ በባህርዳር ስታድየም ይደረጋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ማክሰኞ ፣ ቲፒ ማዜምቤ ደግሞ አርብ ባህርዳር የገቡ ሲሆን ከተማዋም ለጨዋታው እየተዘጋጀች መሆኑን ተዘዋውራ የተመለከተችው ሶከር ኢትዮጵያ ታዝባለች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች በመዞር ጨዋታውን እንዲመለከቱ በድምፅ ማጉያ ሲቀሰቅሰ የቆየ ሲሆን ከትላንት አመሻሽ ጀምሮ የክለቡን መለያ የለበሱ ደጋፊዎች በከተማው ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል፡፡

IMG_4778

የከተማው ህብረተሰብም የጨዋታውን ቀን በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየት የሰጡ ግለሰቦች ተናግረዋል፡፡

በባለሶስት እግር ተሽከርካሪ አገልግሎት ላይ የተሰማራ ወጣት በከተማው በቂ ቅስቀሳ መደረጉን እና ስፖርት አፍቃሪውም ስለጨዋታው ግንዛቤ እንዳለው ይናገራል፡፡

” ስለ ጨዋታው በሚድያ እና በከተማው የተለያዩ ክፍሎች በድምፅ ማጉያ ተነግሯል፡፡ ወጣቱም ከኢትዮጵያ እና ኬንያ ጨዋታ በኋላ ከፍ ያለ ደረጃ ያለው ጨዋታ መመልከት ባለመቻሉ በጉጉት እየጠበቀ ነው፡፡ ” ይላል፡፡ ወጣቱ አክሎም ከተማዋ በሊጉ የሚወክላት ክለብ መጥፋቱ እንደሚቆጫቸው ይገልፃል፡፡ ” ዳሽን ቢራ ባህርዳር ላይ በቋሚነት ይጫወታል ተብሎ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ የትልቅ ስታድየም እና እግርኳስ የሚወድ ህዝብ ባለቤት ሆነን የሚወክለን ክለብ አለማግኘታችን ያንገበግበናል፡፡ ” ይላል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *