ለ2013 የሊጉ አሸናፊ የሚበረከተው ዋንጫ አዲስ አበባ መድረሱ ተገልጿል።
የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት እንደተገባደደ ይታወቃል። የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማዎችም ጊዜያዊ ዋንጫውን በወቅቱ ከመቀበላቸው ባሻገር እስካሁን ድረስ ዋናውን ዋንጫ አለመረከባቸው ጥያቄን ሲያስነሳ ቢከርምም ዛሬ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሁለተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በሚያከናውንበት ሰዓት በዓይነቱ ልዩ ሆኖ የተሰራው ዋንጫ በአሁኑ ሰዓት አዲስ አበባ ቦሌ ዐየር ማረፊያ መድረሱን በሥራ-አስኪያጁ አቶ ክፍሌ ሠይፈ በኩል አስታውቋል።
” አክሲዮን ማኅበሩ ኢትዮጵያን የሚገልፅ ዋንጫ ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ነገር ግን በሀገር ውስጥ ማሠራት አልተቻለም። ብዙ ተቋማት ሞክረን ነበር። በውጪ ሀገራት እንዲሠራም ብዙ ጥረት ተደርጓል። የዚህ አፈፃፀም ላይ ክፍተት ነበር። አሁን ግን ዋንጫው ኤርፖርት ደርሷል። በቀጣይ ቀናት እንረከባለን። የኢትዮጵያን እሴት እና ባህል የሚገልፅ የኛንም ብራንድ የሚገልፅ ዋንጫ አዘጋጅተናል። ” ሲሉ አቶ ክፍሌ የ2013 ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ገልፀዋል።