ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም አንድ ለምንም ተረተዋል።
ተመጣጣኝ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቅ ይታይበት ነበር። በአንፃራዊነት ፍጥነት እና ሀይል የተቀላቀለበተ አጨዋወት መከተል የመረጡት የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በ13ኛው ደቂቃ ከጥሩ ቦታ የቅጣት ምት አግኝተው መሪ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ቦባሲ ብያሩሃንጋ ጫማው አንሸራቶት መሬት ላይ ወድቆም ቢሆን ያገኘውን ኳስ የሚካኤል ሳማኪ መረብ ላይ አሳርፎት ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ወደ ጨዋታው ለመመለስ መታተር የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ አብዛኛውን ደቂቃ ኳስን በመቀባበል መጫወት ይዘዋል። መሪነት ከተወሰደባቸው ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም በረከት ደስታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በሞከረው ኳስ ወዲያው አቻ ሊሆኑ ነበር። ከዚህ የሰላ ሙከራ በተጨማሪ በ26ኛው ደቂቃ ከድር ኩሊባሊ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘው የቅጣት ምት ሲሻማ ግዙፉ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ግብነት ሊቀይረው ነበር። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ይህንን ሙከራ ያደረገው ኦኪኪ እጅግ ጥሩ ኳስ ለበረከት ሰንጥቆለት የመስመር አጥቂው በአስቆጪ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ዩጋንዳዎች ፈጣን የመስመር ላይ ሽግግር በማድረግ ዐፄዎቹን ለማስጨነቅ ቢሞክሩም እምብዛም ሳይሳካላቸው የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቋል።
የያዙትን የኳስ ብልጫ በግብ ማሳጀብ የፈለጉት ፋሲሎች የሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአራተኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሐመድ ከርቀት አክርሮ በመታው ኳስ ወደ ጨዋታው ሊመለሱ ነበር። ነገርግን ታታሪው ተጫዋች የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቷል። በአንፃራዊ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ኳስ የግላቸው አድርገው ለመንቀሳቀስ የሞከሩት የአሠልጣኝ ሚቾ ተጫዋቾ በአጋማሹ ጅማሮ ላይ በቁጥር በርከት ብለው በፋሲል የግብ ክልል ቢገኙም ተጨማሪ ጎል ለማግኘት የሚያስችላቸውን አጋጣሚ መፍጠር አልቻሉም ነበር።
ጨዋታው 63ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ሌላ ግብ ሊያስተናግድ ተቃርቦ ነበር። በዚህ ደቂቃም በተደራጀ መልኩ ወደ ዩጋንዳ የግብ ክልል ያመሩት ፋሲሎች አብዱልከሪም ከመስመር አሻምቶት ኦኪኪ በግንባሩ በሞከረው ኳስ አቻ ለመሆን ጥረዋል። ይህ ሙከራ ከተደረገ ከደቂቃ በኋላ ደግሞ የዩጋንዳው ተጫዋች ኢብራሂም ኦሪት ከወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ቢልከውም የተመታው ጥብቅ ኳስ መዳረሻው የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወደ ውጪ መውጣት ሆኗል።
በተሻለ ተነቃቅተው የገቡትን እና የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው ለመጫወት ያሰቡትን ዩጋንዳዎች ቀስ በቀስ እየበለጡ የመጡት ፋሲሎች አሁንም ኳስን ከመረብ ጋር የሚያዋህድላቸው ተጫዋች ፍለጋ ቀጥለዋል። እርግጥ ቡድኑ ኳሱን ቢቆጣጠርም በተደራጀ መልኩ ተከላካዮቹን አልፎ መግባት ግን እምብዛም አልቻለም ነበር። የሆነው ሆኖ ቡድኑ በመጨረሻ ደቂቃዎቹ ላይም አቻ ሆኖ ከሜዳ የሚወጣበትን ጎል ፍለጋ መታተር ይዟል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከተፈጠሩ አጋጣሚዎችም ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ማስረሻ ከግራ መስመር የተላከለትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ተስፈንጥሮ በግንባሩ ቢሞክረውም ግብ ሳይሆን ቀርቷል። ጨዋታውም በዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አንድ ለምንም አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።
በዛሬው ጨዋታ ፋሲል ከነማን ያሸነፈው የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድንም ነገ ዘጠኝ ሰዓት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሌላ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን አከናውኖ ሰኞ ከኢትዮጵያ እንደሚወጣ ታውቋል።