ከደቂቃዎች በፊት አዲስ አበባ የደረሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስት ተጫዋቾችን ቀንሶ ጁፒተር ሆቴል ማረፊያውን አድርጓል።
ከፊታችን ዓርብ ጀምሮ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠብቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎቹ ከነሐሴ 4 ጀምሮ አዳማ ላይ ዝግጅቱን ሲያደርግ እንደነበር ይታወቃል። ከአዳማው ዝግጅት በተጨማሪ ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ባህር ዳር በማቅናት ከሴራሊዮን እና ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጎ ነበር። አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በልምምድ እና በአቋም መፈተሻ ጨዋታዎቹ ባዩት ብቃት በሚመስል መልኩ ሦስት ተጫዋቾችን በዛሬው ዕለት ከስብስቡ መቀነሳቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
ከስብስቡ የተቀነሱት ተጫዋቾች ዊልያም ሠለሞን፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና በዛብህ መለዮ ናቸው። ከላይ እንደገለፅነው የተጫዋቾቹን ከስብስቡ የመቀነስ ትክክለኛ ምክንያት ባይደርሰንም በአሁኑ ሰዓት ከአጋሮቻቸው ጋር በጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል እንደማይገኙ ተረድተናል።