በመስከረም ወር አጋማሽ ከሩዋንዳ ጋር ላለበት ጨዋታ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቢሸፍቱ ከተማ ጠንካራ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።
በ2022 በኮስታሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የሴቶች የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ሀገራት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎታቸውን መስከረም አጋማሽ ላይ ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ቡድንም ከሩዋንዳ ጋር መመደቡን ተከትሎ አሰልጣኝ ፍሬው ለ35 ተጫዋቾች በቅርቡ ጥሪ በማድረግ በቢሸፍቱ ከተማ ዝግጅቱን ከጀመረ አራት ቀን ተቆጥሯል።
ብሔራዊ ቡድኑ ማረፊያውን ቶሚ ሆቴል በማድረግ በቀን ሁለት ጊዜ ዝግጅቱን በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ሜዳ እየሠራ ይገኛል። የመጀመርያ ጥሪ ከተደረገላቸው 35 ተጫዋቾች መካከል አምስት ተጫዋቾች (ታሪኳ ዴቢሶ፣ ብዙዓየሁ ታደሰ፣ አረጋሽ ካልሳ፣ ትዕግስት ኃይሌ እና ፎዚያ መሐመድ) በሴካፋ ዞን ለካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ከንግድ ባንክ ጋር ኬንያ በመሆናቸው ቡድኑን ሳይቀላቀሉ ቀርተዋል። ሆኖም ክለባቸውን አገልግለው ሲመለሱ ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ጠንከር ያለው የዛሬው የጠዋቱ ልምምድ ትንፋሽን መሠረት ያደረገ ሲሆን አመሻሻሽ በነበረው ልምምድ ደግሞ ኳስ ላይ ትኩረት ያደረገ ሆኖ ሲቀጥል ተመልክተናል። ይህም በቀን ሁለቴ የሚሰሩት ልምምድ ለቀናት እየቀጠለ ሄዶ በቀን አንድ ጊዜ ወደ መሥራት ዝቅ እንደሚል ለማወቅ ችለናል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከሳምንት በኃላ የተወሰኑ ተጫዋቾችን በመቀነስ ከሴካፋ የክለቦች ውድድር የሚመለሱትን ተጫዋቾችን በማካተት የቡድኑን አቅም ለማጠናከር አሰልጣኝ ፍሬው የተለያዩ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ከመስከረም 13-15 ሩዋንዳ ላይ ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከመስከረም 27-29 ኢትዮጵያ ላይ እንደሚደረግ የወጣው መርሐ-ግብር ያመላክታል።