የጋና ብሔራዊ ቡድን አምበል አንድሬ አይው ከዛሬው የኢትዮጵያ ጨዋታ በፊት ሀሳቡን ለጋዜጠኞች ሰጥቷል።
ኳታር ለምታስተናግደው የ2022 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአፍሪካ ሀገራት ካለንበት ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። በምድብ ሰባት ከኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚሙባቡዌ ጋር የተደለደለው የጋና ብሔራዊ ቡድንም ዛሬ ምሽት በኬፕ ኮስት ስታዲየም ዋልያውን በማስተናገድ የምድብ ፍልሚያውን ‘ሀ’ ብሎ የሚጀምር ይሆናል።
ከዛሬው ወሳኝ ጨዋታ በፊትም የጋና ብሔራዊ ቡድን አምበል አንድሬ አይው “ከፊታችን ያሉብንን ሥራዎች በደንብ እናውቃለን። ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርገው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታም በጣም ወሳኝ ነው። ይህንን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታችንን ደግሞ በሜዳችን በጥሩ ውጤት መጀመር እንፈልጋለን።” ብሏል።
የቀድሞ የማርሴ፣ ስዋንሲ፣ ዌስት ሃም እንዲሁም የፊነርባቼ ተጫዋች የነበረው እና በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ አል-ሳድ ያመራው አይው አጠር ያለ ሀሳቡን ሲቀጥል”አሁን ሥራችንን በሚገባ የምንሰራበት ሰዓት ነው። በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ስድስት ጨዋታዎች ይጠብቁናል። የዛሬውን (ከኢትዮጵያ ጋር) ጨዋታ ደግሞ በደጋፊያችን ፊት ማሸነፍ እንፈልጋለን።” በማለት ሀሳቡን አገባዷል።