የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የመጀመርያ ዙር (16 ክለቦች የሚገኙበት ዙር) ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት ሲደረጉ በቅድመ ማጣርያው የሲሸልሱ ሴንት ሚሼል ዩናይትድን 4-1 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፎ ያለፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ80ኛ አመት ክብረ በአሉ ማግስት የወቅቱን የአፍሪካ ሃያል ክለብ ቲፒ ማዜምቤን ያስተናግዳል፡፡ ክለቡ ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ባከናወነበት አፄ ቴዎድሮስ ስታድየም የተገኘችው ሶከር ኢትዮጵያ ከአምበሉ ጋር በጨዋታው ዙርያ አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡
‹‹እድለኝነት ይሰማኛል››
በ1996 ክረምት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለ ወዲህ በ8 የውድድር ዘመናት በአፍሪካ ውድድሮች ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስን ማልያ የለበሰው ደጉ ደበበ እዚህ ደረጃ መድረስ መቻሉ ራሱን እድለኛ አድርጎ እንደሚቆጥር ይናገራል ‹‹ ሁሌም በምትሰራበት ዘርፍ ትልቅ ደረዳ መድረስ የሰው ልጆች ፍላጎት ነው፡፡ እኔም በሃገሪቱ የእግርኳስ ደረጃ መድረስ የሚገባኝን ደረጃ ደርሻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህም እድለኛ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ ››
‹‹ከመደበኛው የተለየ ዝግጅት አላደረግንም››
‹‹ ጥሩ ዝግጅት አድርገናል፡፡ ለዚህ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን እንደማንኛውም መደበኛ የልምምድ ፕሮግራም ነው እየሰራን የምንገኘው፡፡ የሊግ እና የቻምፒየንስ ሊግ ዝግጅት የተለያየ ቢሆንም የተለየ ብለን የሰራነው ልምምድ የለም፡፡ ››
‹‹አላማችን የቲፒ ማዜምቤ ደረጃ ላይ መድረስ ነው››
‹‹ቲፒ ማዜምቤ የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን ነው፡፡ ይህ ግን እኛን ሊያስጨንቀን አይችልም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው፡፡ ትልልቅ ተጫዋቾችንም ይዟል፡፡ እኛም ፍላጎታችን ክለባችንን ልክ እንደ ቲፒ ማዜምቤ ትልቅ ደረጃ ማድረስ ነው እንጂ እነሱን እያሰብን ወደ ኋላ የምናፈገፍግበት ምክንያት አይኖርም፡፡ እንደ ተጋጣሚ እናከብራቸዋለን፡፡ ስራችንንም በአግባቡ እንወጣለን፡፡››
‹‹ጨዋታውን የግድ ማሸነፍ ይጠበቅብናል››
‹‹ ትልቁ ነገር ጨዋታውን ማሸነፍ ነው፡፡ የውድድሩ ባህርይ ጥሎ ማለፍ በመሆኑ በሜዳችን የምናደርገውን ጨዋታ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅብናል፡፡ ከሜዳችን ውጪ የሚያጋጥመንን ስለማናውቅ እዚሁ ጨርሰን መሄድ ይገባናል፡፡ ከሜዳ ውጪ ምን እንደሚፈጠር እንደማይታወቀው ሁሉ በሜዳችንም ምን እንደሚገጥመን አናውቅም፡፡ ቢሆንም አቅማችን የፈቀደውን ነገር ለማድረግ ነው እየተዘጋጀን ያለነው፡፡››