በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ወቅት ጉዳት አስተናግዶ የነበረው የፋሲል ከነማ አማካይ ልምምድ መጀመሩ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የፋሲል ከነማ አማካይ የሆነው ሀብታሙ ተከስተ ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ አዳማ ላይ ልምምድ በሚሰራበት ወቅት ጉልበቱ ላይ ጉዳት አስተናግዶ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል። ጉዳቱን ተከትሎም ተጫዋቹ ብሔራዊ ቡድኑን የተሰናበተ ሲሆን ወዲያው ወደ ክለቡ ፋሲል ከነማ አምርቶ የሚያገግምበትን ሁነት ሲጠባበቅ ነበር።
ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ አማካዩ በግል በጂምናዚየም ራሱን ብቁ ለማድረግ ሲሰራ የነበረውን ልምምድ አጠናቆ በዚህ ሳምንት ሙሉ ለሙሉ ከጉዳት አገግሟል። ይህንን ተከትሎም ተጫዋቹ ከቡድን አጋሮቹ ጋር መደበኛ የሜዳ ላይ ልምምድ መጀመሩ ተመላክቷል። ከዚህም መነሻነት ክለቡ ፋሲል ከነማ ከሱዳኑ አል ሂላል ጋር መስከረም 2 እና 9 ለሚያደርገው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጁ እንደሆነ ታውቋል።