በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ 1ኛ ዙር ጨዋታ ቲፒ ማዜምቤን ነገ ባህርዳር ስታድየም ላይ የሚያስተናገድው ቅዱስ ጊዮርጊስን ጎል የሚጠብቀው ሮበርት ኦዶንካራ ክለቡ ከነገው ጨዋታ በፊት ካደረገው የመጨረሻ ልምምድ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ዩጋንዳዊው ኢንተርናሽናል ሮበርት ኦዶንካራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለነገው ጨዋታ ጥሩ ዝግጅት እንዳደረገ እና በአእምረው ረገድም እንደተዘጋጁ ገልጧል፡፡ ‹‹ለቲፒ ማዜምቤው ጨዋታ ስናደርገው የነበረው ዝግጅታት ጥሩ ነበር፡፡ አሁን የቡድናችን ቅርጽ እና ተነሳሽነት በመልካም ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ማን በጨዋታው ላይ እንደሚሰለፍ ስለማናውቅ ቦታችንን ለማስከበር ጠንክር እየሰራን እንገኛለን፡፡ ሁሉም የቡድን አባላት ከጉዳት ነፃ በመሆናችን ጨዋታውን ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል፡፡ በአእምሮው ረገድም ጥሩ ተዘጋጅተናል፡፡ አሁን በሁላችንም አእምሮ ውስጥ ያለው ጨዋታውን ማሸነፍ ነው፡፡ ›› ብሏል፡፡ ሮበርት አክሎም ለቲፒ ማዜምቤ የተጋነነ ክብር እንደማይሰጡ ተናግሯል፡፡
‹‹ ቲፒ ማዜምቤን ጥለን ለማለፍ የምንችለውን ያህል እናደርጋለን፡፡ በነገው ጨዋታ የሜዳ እና የደጋፊ አድቫንቴጅ ይኖረናል፡፡ ይህንንም መጠቀም ይኖርብናል፡፡ ቲፒ ማዜምቤ ጠንካራ ክለብ በመሆኑ ብናከብራቸውም ከሚገባው በላይ የተጋነነ አክብሮት አይኖረንም፡፡ ምክንያቱም እኛ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነን፡፡ የነገው ጨዋታ ጥካራ ቢሆንም የሜዳችንን አድቫንቴጅ በሚገባ ተጠቅመን ወደ ሉሙምባሺ ለመጓዝ ተዘጋጅተናል፡፡
‹‹ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቲፒ ማዜምቤን የመከታተል እድል አጋጥሞኛል፡፡ ምርጥ ተጫዋቾችን ያሰባሰበ ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን እንደ ትልቅ ነገር አንመለከተውም፡፡ ሜዳ ላይ የምንገባው 11ለ11 ሆነን ነው፡፡ ጨዋታውን አቅልለን እንጫወታለን፡፡ ጥቃቅን ስህተቶች ላለመስራት ተጠንቅቀን እንጫወታለን፡፡ የሜዳችንን እና የደጋፊያችንን አድቫንቴጅ ተጠቅመንም እናሸንፋለን፡፡››
በ2003 አጋማሽ ፈረሰኞቹን ከተቀላቀለ በኋላ አስተማማኝ ግብ ጠባቂነቱን በማስመስከር በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከሚዘመርላቸው ተጫዋቾች አንዱ ሆኗል፡፡ በነገው እለትም ደጋፊዎቹ የቡድኑ የጅርባ አጥንት እንደመሆኑ እምነቱን ገልጧል፡፡
‹‹ በማንኛውም ጨዋታ የሜዳን አድቫንቴጅ መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ እግርኳስን ስትጫወት ከጀርባህ ደጋፊዎችን ማግኘት ሁልጊዜም የበለጠ እንድትጫወት ያነሳሳሃል፡፡ ብትደክም እንኳን ተነቃቅተህ እንደገና ወደ ጨዋታው እንድትመለስ ይረዳሃል፡፡ እናም በደጋፊዎቻችን ታግዘን ቲፒ ማዜምቤዎችን ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ አድርገን እናሸንፋለን፡፡›› ሲል ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡