በትናንትናው ዕለት በይፋ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም የጀመረው አዲስ አዳጊው ክለብ ከደቂቃዎች በፊት ናይጄሪያዊ አማካይ የግሉ አድርጓል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ አሸናፊ በመሆን የሀገሪቱን ከፍተኛ የሊግ እርከን የተቀላቀለው አዲስ አበባ ከተማ አስራ አንድ አዳዲስ ተጫዋቾችን በትናንትናው ዕለት ማስፈረሙን መዘገባችን ይታወቃል። ድረ-ገፃችን አሁን ባገኘችው መረጃ ደግሞ ክለቡ ናይጄሪያዊውን አማካይ ቻርለስ ሪባኑን አስፈርሟል።
በሀገሩ ናይጄሪያ ዲያፋ አካዳሚ ውስጥ ሲጫወት ቆይቶ በ2013 በከፍተኛ ሊግ የሚወዳደረውን ሀምበሪቾ ዱራሜን ተቀላቅሎ የነበረው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቻርለስ ሪባኑ በአሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ዐይን ውስጥ ገብቶ አዲስ አዳጊውን ክለብ ተቀላቅሏል። ዝውውሩን ለማገባደድ ከትናንት በስትያ ምሽት አዲስ አበባ የደረሰው ተጫዋቹም ከደቂቃዎች በፊት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመገኘት የአንድ ዓመት ውል መፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።