በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር በአንድ ምድብ የሚገኘው የጋና ብሔራዊ ቡድን ቻርለስ አኮኖርን ካሰናበተ በኋላ የቀድሞ አሠልጣኙን ለመቅጠር ከጫፍ ደርሷል።
ኳታር ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ሰባት የተደለደለው የጋና ብሔራዊ ቡድን በቅርብ ጊዜ እያስመዘገበ ባለው ውጤት ቻርለስ አኮኖርን ከትናንት በስትያ ማሰናበቱ ተሰምቶ ነበር። በቦታው ሰው ለመተካት የ72 ሰዓት ቀነ ገደብ ያስቀመጠው የሀገሪቱ እግርኳስ ፌዴሬሽን በዛሬው ዕለት የቀድሞ አሠልጣኙ ሚሎቫን ራጄቫክን ለመመለስ መወሰኑ ታውቋል።
በ2008 የአፍሪካ ዋንጫ እስከ ፍፃሜ የደረሰውን እና በ2010 ዓለም ዋንጫ አስደናቂ ጉዞ በማድረግ እስከ ሩብ ፍፃሜ የተጓዘውን ቡድን የመሩት ሚሎቫን ራጄቫክ ከጥቋቁር ከዋክብቶቹ ጋር ከተለያዩ በኋላ የሳውዲ አረቢያውን አል አህሊ፣ የስሎቬኒያውን ሩዳ ቬሌንጄ እንዲሁም የኳታሩ፣ አልጄሪያ እና ታይላንድ ብሔራዊ ቡድኖችን አሰልጥነዋል። የጋና ብዙሃን መገናኛዎች አመሻሽ ላይ እያወጡት ባለው መረጃም የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚሎቫን ራጄቫክን ለማምጣት መወሰናቸውን እያስነበቡ ይገኛሉ። የሚሎቫን ራጄቫክ ረዳቶች በመሆን ደግሞ ኦቶ ኦዶ እና ጆርጅ ቦአቴንግ እንደሚቀጠሩ ተሰምቷል።