ረሂማ ዘርጋው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀውን ክለብ ተቀላቅላለች፡፡
የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ከሻምፒዮኑ ንግድ ባንክ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን በሊጉ ይዞ ማጠናቀቅ የቻለው መከላከያ ለ2014 የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ (መቶ አለቃ) ስለሺ ገመቹ እየተመራ ከወራት በፊት ከአስር በላይ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቿ ረሂማ ዘርጋውን የግሉ ማድረጉ እርግጥ ሆኗል፡፡
ረሂማ ዘርጋው በተክለሀይማኖት ፔፕሲ እግር ኳስን ከጀመረች በኋላ በመቀጠል ወደ ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ በማምራት እስከ 2002 ድረስ ግልጋሎት ከሰጠች በኋላ ነበር ክለቡ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሸጡን ተከትሎ ተጫዋቿም ወደ ክለቡ አምርታ በአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው በሚመራው ንግድ ባንክ ውስጥ የተሳኩ 11 ዓመት መቆየት የቻለችው። በተጠናቀቀው የውድድር አመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አሸናፊ በሆነው ንግድ ባንክ የመጨረሻ ቆይታን በማድረግ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች በመባል የተመረጠችው አጥቂዋ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ማረፊያዋን መከላከያ አድርጋለች።