ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነውን መርሐ-ግብር ለመዳኘት አራት እንስት የሀገራችን ዳኞች ወደ ናይሮቢ ሊያመሩ ነው።
በቀጣይ ዓመት በኮስታሪካ አስተናጋጅነት በሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታቸውን ካለንበት ሳምንት አንስቶ ማድረግ ይጀምራሉ። ካሉት መርሐ-ግብሮች መካከል ደግሞ መስከረም 15 ኬንያ እና ዩጋንዳ ናይሮቢ ላይ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ይጠቀሳል።
ይህንን ጨዋታም በቅርቡ በሴካፋ ውድድር ላይ ጨዋታዎችን ስትመራ የነበረችው አልቢትር አስናቀች ገብሬ በመሐል ዳኝነት እንደምትመራው ታውቋል። ከአስናቀች በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን የመምራት የተሻለ ልምድ ያላት ወይንሸት አበራ እና እንደ ዋና ዳኛዋ ሁሉ ለሴካፋ ውድድር ወደ ኬንያ አምርታ የነበረችው ይልፋሸዋ አየለ በረዳትነት ተመርጠዋል። ከሦስቱ እንስቶች በተጨማሪ ደግሞ ከአስራ አንድ ቀናት በፊት የደቡብ ሱዳኑ አትባራ እና የሱዳን አል ሃሊ ሜሮዌ ያደረጉትን የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት የመራችው ሊዲያ ታፈሰ የጨዋታው አራተኛ ዳኛ በመሆን ወደ ስፍራው እንደምታመራ ተመላክቷል።