የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን ተሳታፊው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስት ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ብርቱ ተፎካካሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለ2014 የውድድር ዘመን ቀደም ብሎ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔን ኮንትራት በሁለት ዓመት ካደሰ በኋላ ከአንድ ወር በፊት ከተለያዩ ክለቦች ስድስት አዳዲስ ፈራሚዎችን ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን በማከል የአዳዲስ ፈራሚዎችን ቁጥር ወደ ዘጠኝ አሳድጓል፡፡
ቤተልሄም አስረሳኸኝ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ፊርማዋን ያኖረች አዲሷ ፈራሚ ሆናለች፡፡ የቀድሞዋ የአዳማ ከተማ የግራ መስመር ተከላካይ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት ወደ ጌዲኦ ዲላ አምርታ በመጫወት ያሳለፈች ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ሌላኛው የዲቪዚዮኑ ክለብ ኤሌክትሪክ አምርታለች፡፡
አጥቂዋ ትንቢት ሳሙኤል ሌላኛዋ የክለቡ አዲስ ፈራሚ ነች። ከዚህ ቀደም ለጌዲኦ ዲላ እና አቃቂ ቃሊቲ ስትጫወት የምናውቃት ተጫዋቿ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ በትግራይ አካባቢ በተፈጠረ ወቅታዊ ችግር የተነሳ ለፈረመችበት ክለብ መቐለ 70 እንደርታ መጫወት ባለመቻሏ እስከ መጋቢት ወር ድረስ ሳትጫወት ቆይታ በመጨረሻም ወደ ድሬዳዋ ዓምርታ አመቱን ማጠናቀቅ ችላ ቀጣዩ ማረፊያዋ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሆኗል፡፡
ንቦኝ የን ሌላኛዋ የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ተጫዋች ነች፡፡ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከተገኘች በኋላ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታ የነበራት ሲሆን ተጫዋቿም በክለቡ ብዙም ግልጋሎት ስትሰጥ አልተመለከትናትም። አሁን ከክለቡ ጋር የነበራት ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ቀይ እና ነጭ ለባሾቹን መቀላቀል ችላለች፡፡