ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለቦች የተዘጋጀው አዲሱ ዋንጫ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ኃይሌ ሪዞርት በተዘጋጀ ፕሮግራም በይፋ ለዕይታ በቅቷል።
ከምሽቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በሀዋሳ ኃይሌ ሪዞርት በተሰናዳው መርሐ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የኢትዮጵያ ፕሪምየር አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ፣ የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተወካይ አቶ ጌታቸው እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች እና የብዙሃን ባለሙያዎች ተገኝተዋል። በዝግጅቱ ጅማሮ ላይ የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሠብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል። በመቀጠል ደግሞ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ በሊጉ ውድድር የታየውን በጎ ነገር አድንቀው በቀጣይም የበለጠ ነገር ለማግኘት እና ለማሳካት ጥረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ዋናው የሊጉ ዋንጫ ከመተዋወቁ በፊት የፕሪምየር ሊጉ አዲስ የማጀቢያ ሙዚቃ እና ሎጎ በስፍራው ለተገኙ እንግዶች ይፋ የተደረገ ሲሆን በማስከተል ደግሞ አቶ ኢሳይያስ እና መቶ አለቃ ፍቃደ ከሳምንታት በፊት ሀገራችን የገባውን ዋንጫ ለዕይታ አብቅተዋል። ለንደን ላይ የተለያዩ ትላልቅ ዋንጫዎችን የመሥራት ልምድ ባለው ተቋም ተሰርቶ የመጣው ይህ ዋንጫ 12 የተለያዩ የሀገራችንን ባህል፤ ተፈጥሮ እና ታሪክለማስተዋወቅ የሚረዱ ይዘቶች እንዳሉበት ተጠቁሟል። በዚህም በዋንጫው ላይ የዋልያ፣ የሰሜን ተራሮች፣ የላሊበላ፣ የኮንሶ፣ የዓባይ ግድብ፣ የጥያ ትክል ድንጋይ፣ የፋሲለደስ፣ የአክሱም፣ የጀጎል በር፣ የሉሲ፣ የሶፉ ኡመር እና የጋሻ ምስሎች እንዲኖረው ተደርጎ መሠራቱም ታውቋል። ለንደን ላይ መቀመጫውን ያደረገው ቶማስ ላይት ተሰርቶ የመጣውም ዋንጫ ለዕይታ በቅቷል።