በመክፈቻው ዕለት ሁለተኛው ጨዋታ ላይ ጥቂት ሀሳቦችን እነሆ !
በአምናው ውድድር መሀል ላይ ወደ ሊግ አሰልጣኝነት የተመለሱት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ እና አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ምሽት ላይ በሁለተኛው ጨዋታ ይገናኛሉ። የድሬው አሰልጣኝ ዘማርያም 2013 ላይ መጠገን የጀመሩትን ቡድን ዘንድሮ በራሳቸው መልክ ይዘው ሲመጡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ደግሞ ከአዲሱ ቡድናቸው ወላይታ ድቻ ጋር ዓመቱን ይጀምራሉ።
በጨዋታው ኳስ ተቆጣጥሮ ለማጥቃት የሚሞክር ድሬዳዋ ከተማ እንድሁም በተደራጀ መከላከል ቆይቶ ከሜዳው በቶሎ ለመውጣት የሚጥር ወላይታ ድቻ ልንመለከት እንችላለን።
ፌደራል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ተመድበዋል።
የድሬዳዋ ከተማው ያሲን ጀሚል በመጠነኛ ጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሲሆን የወላይታ ድቻ መስመር ተከላካይ ያሬድ ዳዊት በቅጣት አይሰለፍም። ሌላው የድቻ ወሳኝ ተጫዋች ስንታየው መንግሥቱም በጉዳት ምክንያት የመሰለፍ አለመሰለፉ ሁኔታ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡
ቡድኖቹ እስካሁን በሊጉ ለ10 ጊዜያት ተገናኝተው ብርቱካናማዎቹ አምስት ጊዜ ባለድል መሆን ሲችሉ የጦና ንቦቹ ለመጀመሪያ ጊዜ አምና 3-1 ማሸነፍ ችለዋል። ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ። በጨዋታዎቹ ድሬ 11 ፣ ድቻ 7 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
የሁለቱን ክለቦች የክረምት ወቅት ዝግጅት እና በቀጣይ የሚኖራቸውን መልክ በሰፊው ያወሳንባቸውን ፅሁፎች ከዚህ በታች ያገኛሉ።
ድሬዳዋ ከተማ
https://soccerethiopia.net/football/7142911
ወላይታ ድቻ
https://soccerethiopia.net/football/7167611