ጥሩ ፉክክር ባስተናገደው የዛሬው ቀዳሚ ጨዋታ ፋሲል ከነማ በፍቃዱ ዓለሙ ሦስት ግቦች ሀዲያ ሆሳዕናን 3-1 መርታት ችሏል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ቻምፒዮኖቹ ፋሲል ከነማዎች በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ የገባው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋና ዋንጫ ተረክበዋል።
በሁለቱም ተጋጣሚዎች በኩል የማጥቃት ፍላጎት እየታየበት በጀመረው ጨዋታ ሆሳዕናዎች ይበልጥ አስፈሪ ሆነው ታይተዋል። ቡድኑ የተጋጣሚው ቅብብሎች ከመሀል ሜዳ እንዳያልፉ በማድረግ ከአማካዮቹ በሚሰነጠቁ ኳሶች ወደ ቀኝ አድልቶ በጊዜ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን ፈጥሯል። በመስመር ተከላካዩ ብርሀኑ በቀለ እና በዛው መስመር በተሰለፈው አጥቂው ፀጋዬ ብርሀኑ ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም የፀጋዬ ሁለተኛው ሙከራ ሚኬል ሳማኬን የፈተነ ነበር።
17ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስም እንዲሁ በሳማኬ ጥረት የዳነ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን ፋሲሎች ቀስ በቀስ ከሜዳቸው እየወጡ ቀጥተኛነትን የቀላቀለ የማጥቃት ሂደትን አሳይተውናል። በተለይም ከሱራፌል ዳኛቸው በቀጥታ ወደ ፊት ይጣሉ የነበሩ ኳሶች አደጋ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ምልክቶች ታይተዋል። 25ኛው ደቂቃ ላይም አማካዩ ወደ ቀኝ ያሻገረውን ኳስ ሰዒድ ሁሴን ወደ ሳጥን ውስጥ ሲልከው አጥቂው ፍቃዱ ዓለሙ በሆሳዕና ተከላካዮች መሀል በመውጣት ቀለል አድርጎ ግብ አድርጎታል።
ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው ወደ መመጣጠን የመጣበት ነበር። ፋሲሎች ኳስ ይዘው ወደ ሆሳዕና ሜዳ በመግባት እንዲሁም አልፎ አልፎ ረዘም ያሉ ኳሶችን በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ጥረዋል። ሆሳዕናዎችም በፋሲል ሦስት የመሀል ተከላካዮች ጎን በተለይም በቀኙ በኩል አድልተው ሙከራዎችን ለማድረግ ጥረዋል። ቡድኑ በጥሩ የማጥቃት ሂደት ወደ ሳጥን ቢቃረብም የመጨረሻ የቅብብል ጥራት መውረድ ከባድ ሙከራዎችን እንዳያደርግ ምክንያት ሆኗል።
በሙከራ ረገድ ፋሲሎች ይበልጥ አሰገኛ ሆነው ሲታዩ 40ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ከሱራፌል በተነሳ ኳስ በረከት ደስታ በግራ በኩል ሰብሮ በመግባት ያደረገው ሙከራ በመስይ አያኖ ድኗል። ግብ ተባቂው የሱራፌል ዳኛቸውን የርቀት ቅጣት ምት ከባድ ሙከራም አድኗል። ሆኖም ዕረፍት ለመውጣት ሲቃረቡ ከሱራፌል የተነሳውን ረጅም ኳስ ፍቃዱ ዓለሙ በግራ የሳጥኑ ክፍል ይዞ በመገባት ቆርጦ ወደ ግብ ሲልከው መሳይ ወደ ውጪ ወጥቷል ብሎ በመዘናገቱ ሁለተኛ ግብ ተቆጥሮበታል።
ከዕረፍት መልስ ሁለት ደቂቃዎች እንዳለፉ ሀዲያ ሆሳዕና ግብ አስቆጥሯል። ከእጅ ውርወራ የተነሳውን ኳስ ከፀጋዬ የተቀበለው ባዬ ገዛኸኝ በአስደናቂ ሁኔታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት በሳማኬ መረብ ላይ አሳርፏል። ጥሩ ፉክክር እየታየበት በቀጠለው ጨዋታ ሆሳዕናዎች የተሻለ ኳስ ይዘው ክፍተቶችን ሲፈልጉ ፋሲሎች በፍጥነት ተጋጣሚያቸው ደጃፍ ለመግባት ጥረዋል። በሁለቱም በኩል በፍቃዱ እና ባዬ የተደረጉ የግንባር ሙከራዎች ወደ ውጪ ሲወጡ 65ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ኡመድ ዑኩሪ ባዬ ካስቆጠረበት ቦታ ላይ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወጥቷል።
በዛብህ መለዮ እና ኤፍሬም ዘካሪያስ ተቀይረው የገቡበት ጨዋታ ተጋጣሚዎቹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ለማግኘት ተፋልመዋል። በሆሳዕና በኩል በተፈጠረ አደገኛ አጋጣሚ 75ኛው ደቂቃ ላይ ዑመድ ኡኩሪ በቀኝ በኩል ሰብሮ ሲገባ በያሬድ ባየህ ጥፋት ተሰርቶብኛል ብሎ ቢወድቅም ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በዝምታ አልፈውታል። በበረከት እና ሱራፌል ከረጅም ረቀት ሙከራዎችን ያደረጉት ፋሲሎች 83ኛው ደቂቃ ላይ በግራ በኩል በበረከት ደስታ በሰነዘሩት ጥቃት ተጫዋቹ ሳጥን ውስጥ በኤልያስ አታሮ ጥፋት ተሰርቶበት ፍፀም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ፍቃዱ ዓለሙም አጋጣሚውን ሦስተኛ ግብ አድርጎት የዘንድሮውን የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ ሰርቷል።
ይህ ከሆነ ሦስት ደቂቃዎች በኋላ ኤፍሬም ዘካሪያስ በበዛብህ መለዮ ላይ በሰራው ጥፋት የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል። በመጨረሻ ደቂቃዎች ትኩረት ሳቢ ሁነቶችን ያስተናገደው ጨዋታም በፋሲል ከነማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።