ጥሩ ፉክክር የተደረገበት የባህር ዳር ከተማ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ባህር ዳሮች ከሁለተኛው ሳምንት ጨዋታቸው አንፃር ፍቅረሚካኤል ዓለሙን በአብዱልከሪን ንኪማ በመተካት ወደ ዛሬው ጨዋታ ሲመጡ ወልቂጤዎች ደግሞ ያሬድ ታደሰ እና አበባው ቡጣቆን በረመዳን የሱፍ እና አህመድ ሁሴን በመቀየር ሁለት ለውጦችን አድርገዋል።
በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ተመሳሳይ አጨዋወት ያላቸው ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከጅምሩ ተፈታትነዋል። የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር በተቸገሩባቸው ደቂቃዎች የማጥቃት ሂደታቸው ወደ መስመሮች ያደላ ነበር። ሆኖም በግራ እና በቀኝ የነበራቸው መመጣጠን አንዳቸው ከአንዳቸው የተሻለ ሰብሮ የመግባት አጋጣሚ መፍጠር ከብዷቸዋል። ነገር ግን 20ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታው የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ ሆኗል። ጌታነህ ከበደ ከሳጥን ውጪ ከጫላ ተሺታ የተቀበለውን ኳስ የመጀመሪያ ንክኪውን በማሳመር ሳይታሰብ አክርሮ በመምታት በድንቅ ሁኔታ በባህር ዳር መረብ ላይ አሳርፏል።
ከግቡ በኋላ ባህር ዳሮች በመጠኑ መሻሻል አሳይተው ወደ ተጋጣሚያቸው ሜዳ አድልተው መሀል ለመሀል ጥቃቶችን ለመሰንዘር ቢሞክሩም የቡድኑ አደገኛ አጋጣሚ የታየው 34ኛው ደቂቃ ላይ ነበር።
የሰለሞን ወዴሳ ተሻጋሪ ኳስ ከቀኝ አቅጣጫ ወደ ሳጥን ሲደርስ በተከላካዮች በአግባቡ ሳይርቅ ቀርቶ ኦሴይ ማዉሊ ከግቡ አፋፍ ላይ ግልፅ ዕድል ቢያገኝም ወደ ላይ ሰዶታል። በሂደት ጨዋታውን ወደ መመጣጠን በመመለስ ወደ ግራ አድልተው ማጥቃት የሞከሩት ወልቂጤዎች በበኩላቸው 40ኛው ደቂቃ ላይ መሀል ለመሀል ጥቃት ሰንዝረው በኃይሉ ተሻገር ጥሩ ኳስ ከግራ ለሚነሳው ጫላ ተሺታ ቢያሳልፍለትም አጥቂው ሚዛኑን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር የአአራደር እና የተጫዋቾች ሚና ለውጥ ያደረጉት ባህር ዳሮች ጫና ነመፍጠር ጀምረዋል። ከግራ መስመር ተመላላሽነት በዛው መሰር ወደ አማካይነት የተለወጠው ግርማ ዲሳሳ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ወደ ግብ ለመላክ የሞከረውን ካስ ዳግም ንጉሴ በእጅ በመንካቱ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይም ፍፁም ዓለሙ አጋጣሚውን ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ አድርጓል።
አቻ ከሆኑ በኋላም ባህር ዳሮች ወደ ቀኝ ባደላ ጥቃት የወልቂጤን የግራ መስመር መፈተን ቀጥለው ነበር። ሆኖም ጫናው ሌሎች ዕድሎችን መፍጠር ከመጀመሩ አስቀድሞ ወልቂጤዎች ወደ ማጥቃቱ ተመልሰዋል። አብዱልከሪም ወርቁን በጉዳት ብበፋሲል አበባየሁ የቀየሩት ወልቂጤዎች በጫላ ተሺታ ምትክም አላዛር ዘውዱን አስገብተዋል። የቡድኑ የማጥቃት ሂደት የቆሙ ኳስ ዕድሎችን ይዞ መምጣት የጀመረ ሲሆን የተሻለ በነበረው አጋጣሚ 68ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ የበኃይሉን በአጭር የተጀመረ የማዕዘን ምት ከሳጥን ውስጥ ቢሞክርም ፋሲል ገብረሚካኤል በቀላሉ ይዞበታል።
ከሁለተኛው የውሀ ዕረፍት በኋላ የቡድኖቹ የማጥቃት ሂደት ተመጣጥኖ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ ጀምረዋል። ወልቂጤዎች በተሻለ ኳስ ቁጥጥር እና ረዘም ያሉ ካሶችን ወደ ሳጥን ሲጥሉ ባህር ዳሮች ይበልጥ የመልሶ ማጥቃት ባህሪ ታይቶባቸውል። ሳለአምላክ ተገኘ እና መሳይ አገኘሁን በማስገባትም ፊት ላይ ያለውን የመስመር ጥቃታቸው ክፍል በአዲስ ጉልበት አድሰዋል። ወደ ቀኝ በማድላትም ክፈተት ለማግኘት ጥረዋል። ሆኖም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ወደ ሳጥን የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ባይታጡም አደገኛ ሙከራዎችን ሳንመለከት ጨዋታው 1-1 እንዲጠናቀቅ የግድ ሆኗል።
ውጤቱን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማዎች 6 ነጥብ ካሳኩ አምስት ቡድኖች መካከል በአንድ ከፍ ብለው በአንደኝነት ሲቀመጡ ወልቂጤ የደረጃ ለውጥ ባያመጣም ነጥቡን ወደ ሁለት አሳድጓል።