የነገውን ቀዳሚ ጨዋታ የተመለከቱ ጉዳዮችን በዳሰሳችን ተመልክተናል።
በተመሳሳይ ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያላቸው ቡና እና ሰበታ እርስ በእርስ በሚገናኙበት ጨዋታ ከባለ አራት ነጥቦች ጎራ ለመቀላቀል ይፎካከራሉ። በመጀመሪያው ሳምንት ከተጋጣሚዎቻቸው ጠንከር ያለ ፈተና ገጥሟቸው የነበረ ቢሆንም ነጥብ መጋራት ችለው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች በቀጣዩ ሳምንት ግን ሽንፈት አስተናግደዋል። ከሽንፈት ባለፈ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውም ተዳክሞ መታየቱ በነገው ጨዋታው ብዙ ተሻሽለው መቅረብ እንዲኖርባቸው መልዕክት ያስተላለፈ ነበር።
በሸገር ደርቢ ሰፊ ሽንፈት የገጠመው ኢትዮጵያ ቡና አሁንም ከሜዳው ከኳስ ጋር በነፃነት የመውጣት ፈተናው እንደቀጠለ ነው። ከመጫወቻ ሜዳው ምቹ አለመሆን ጋር ተዳምሮ የተከላካይ መስመር ቅብብሎቹ መልሰው ራሱ ላይ አደጋ ሲያመጡም መመልከት ችለናል። ቡድኑ አልፎ አልፎ ረዘም ያሉ ኳሶችን በመጣል ወደ ቀጣዩ አጋማሽ ለመግባት ጥረቶች ሲያደር ቢታይም በአጥጋቢ ሁኔታ ችግሩን የቀረፉለት አይመስልም። በነገው ጨዋታ ተጋጣሚው ወደ ኋላ ቀርቶ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ለመድረስ ፍላጎት ካሳየ ቡና ከራሱ አጋማሽ ለመውጣት በንፅፅር የቀለለ ፈተና ሊገጥመው ቢችልም ያ ካልሆነ ግን የመስመር አጥቂዎቹን የኋልዮሽ እንቅስቃሴ ከአማካዮቹ ኳስ የመቀበያ ክፍተቶችን የመፈለግ ጥረት ጋር በማጣመር ለችግሩ መፍትሄ መፈለግ ሳይኖርበት አይቀርም።
ሰበታዎች በሁለቱ ጨዋታዎች የተለያየ መልክ ነበራቸው። በመከላከያው ጨዋታ ወደ ፊት ገፍተው ለማጥቃት ያደረጉት ጥረት አተገባበሩ ደካማ ቢሆንም በቀዳሚው የጊዮርጊስ ጨዋታ ግን የግብ ክልላቸው በቀላሉ እንዳይደፈር ማድረግ ላይ ስኬታማ መሆን ችለው ነበር። ምንም እንኳን ጊዮርጊስን በጥልቀት ወደ ኋላ ሸሸት ብለው የተከላከሉበትን መንገድ ከቡና ጋር ሊቀይሩ ቢችሉም አጠቃላይ አቀራረባቸው ኳስ መያዝ የሚያዘወትረው ተጋጣሚያቸው ክፍተት እንዳያገኝ ማድረግ ላይ ሊያተኩር የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። ቡድኑ የተከላካይ ክፍሉን በጥቂቱ ወደ መሀል ስቦ ከፊት ጀምሮ ጫና ያሳድራል ወይንስ በራሱ ሜዳ ቆይቶ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ያነፈንፋል የሚለው ነጥብ ግን ከላይ ካነሳነው የቡና ኳስ ይዞ የመውጣት ችግር ጋር ሲገናኝ በሚፈጥረው ውጤት የጨዋታውን አጠቃላይ ፍሰት የሚወስነው ይመስላል።
ሁለቱ ተጋጣሚዎች በማጥቃቱ ረገድ ደካማ ሆነው ነው የሚገናኙት። ኢትዮጵያ ቡና ባለፈው ዓመት ደጋግሞ ሲያደርገው እንደነበረው የመስመር ተከላካዮቹን ጨምሮ በርከት ያሉ ተሰላፊዎቹን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚያደርስበት አኳኋን ዘንድሮ ተገድቦ ተመልክተነዋል። አማካይ ክፍሉ በታፈሰ ሰለሞን እንቅስቃሴ ላይ በጣም የተመረኮዘ ሲመስል የግራው የአቡበከር ናስር መስመርም በአመዛኙ የጥቃቱ መቋጫ ሲሆን ይታያል። ይህ ሁኔታ ቡናን ተገማች እያደረገው ክፍተቶች በቶሎ ሲዘጉበት መመልከትም ችለናል። ሰበታ ከተማም መልሶ ማጥቃትን በመረጠበት ጨዋታ ፊት ላይ ያለቅጥ ሳስቶ ሙከራዎችን ማድረግ ሲያዳግተው ስንመለከት የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ባሳየበት የመከላከያው ጨዋትም በመስመር አጥቂዎቹ በኩል ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረገው ጥረት የተሳካ አልነበረም።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ቡና በነገው ጨዋታ በቶሎ ከሜዳ መውጣት የመስመር ተከላካዮችን ጭምር ባሳተፈ መልኩ ተጋጣሚ ሳጥን ዙሪያ መድረስ ላይ ተሻሽሎ መቅረብ የግድ ይለዋል። አቡበከርን ወደ መሀል አጥቂነት ማምጣትም ከአንተነህ ተስፋዬ ቅጣት በኋላ ደካማ ጥምረት የታየበትን የሰበታ የመሀል ተከላካይ ክፍል ከመፈተን ባለፈ እንደአምናው ለመስመር አጥቂዎች ክፈተት ሊሰጥ የማጥቃት አማካዮቹም ወደ ሳጥን እንዲገቡ ስራ ሊያቀልላቸው ይችላል። በሰበታ በኩል ከፊት ጫና ማሳደርንም ሆነ ከኋላ መጠቅጠቅን ይምረጥ የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ለቡና ቅብብሎች ክፍተት የማይሰጡ ሆነው መገኘት የግድ ይላቸዋል። እስካሁን ኳስ እና መረብ ያላገናኘው ሰበታ የጁኒያስ ናንጄቦን ፍጥነት ያማከለ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ለጨዋታው ይዞ መግባትም የማጥቃት ዕቅዱ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ የማይቀር ነው።
ኢትዮጵያ ቡና ከመሀል ተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጄ ውጪ ቀሪ ስብስቡ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል። በሰበታ በኩል አንተነህ ተስፋዬ የቀይ ካርድ ቅጣት ላይ ሲገኝ መሀመድ አበራ ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና አክሊሉ ዋለልኝም ከቡድኑ የጉዳት ዝርዝር ውስጥ አልወጡም።
ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ዳንኤል ግርማይ በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ከእስካሁኑ ስምንት ግንኙነታቸው ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ሰበታ ከተማ ደግሞ ሁለት ድሎችን አስመዝግበዋል። ቀሪ ሦስት ጨዋታዎቻቸው ላይ ነጥብ ሲጋሩ ቡና ዘጠኝ ሰበታ ሰባት ኳሶችን ከመረብ ማገናኘት ችለዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
አቤል ማሞ
ኃይሌ ገብረትንሳኤ – ወንድሜነህ ደረጄ – ቴዎድሮስ በቀለ – አስራት ቱንጆ
ዊሊያም ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሠ ሰለሞን
ሚኪያስ መኮንን – እንዳለ ደባልቄ – አቡበከር ናስር
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ለዓለም ብርሃኑ
ጌቱ ኃይለማርያም – በረከት ሳሙኤል – ቢያድግልኝ ኤሊያስ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ክርዝስቶም ንራምቢ – በኃይሉ ግርማ
ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ
ጁኒያስ ናንጄቤ