አዞዎቹን ከነብሮቹ የሚያገናኘው የሦስተኛውን ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።
ሊጉን በሽንፈት ጀምረው የነበሩት ሁለት ቡድኖች በዚህ ሳምንት የሚደረጉ ጨዋታዎችን ያሳርጋሉ። እርግጥ ነው አርባምንጭ ከተማ በሁለተኛው ሳምንት አዲስ አበባን በመርታት ማገገም ችሏል። ሀዲያ ሆሳዕና ግን ተጨማሪ ሽንፈት አስተናግዶ ነው ለነገው ጨዋታ የሚደርሰው። በመሆኑም ውጤት ይዞ የመውጣት ጫናው ወደ ሀዲያ ሆሳዕና ያጋደለበት እና አርባምንጮች ተከታታይ ድል ለማግኘት ወደ ሜዳ የሚገቡበት የጨዋታ ሂደት ይጠበቃል።
አርባምንጭ ከተማ እና አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በአዲስ አበባው ድል ለነበረባቸው የደጋፊ ጫና ምላሽ መስጠት ችለዋል። ድሉ ከኋላ በመነሳት የተገኘ መሆኑም ሲታይ ቡድኑ በሥነልቦናው ረገድ ለነገው ጨዋታ ተጨማሪ ትርፍ ማግኘቱን መገንዘብ ይቻላል። አርባምንጭ ከመጀመሪያው ጨዋታ አምስት ለውጦችን ከማድረጉ ባለፈ በሁለተኛው አጋማሽ በድጋሚ ያደረጋቸው ቅያሪዎች ውጤት ለማምጣት ሲያበቃው መመልከታችን ደግሞ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለቀጣይ ጨዋታዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሙትን ምርጥ 11 በመለየቱ ረገድ ምልክት የሰጣቸው ይመስላል። በመሆኑም ነገ በእነዚህ ነጥቦች እና የወረቀት ሥራቸው ባለቁ ዜጋ ተጫዋቾቹ የተቃኘ ቀዳሚ አሰላለፍ ከአርባምንጭ ከተማ እንጠብቃለን።
ሀዲያ ሆሳዕናን የሁለቱ ጨዋታዎች ውጤት ይገልፁታል ማለት ይከብዳል። እርግጥ ነው በሁለቱም ላይ የተሰሩ ስህተቶች ዋጋ ቢያስከፍሉትም ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማን አከታትሎ ማግኘቱም ከተጋጣሚ ክብደት አንፃር ቀላል የሚባል አይደለም። አምና ከሀዋሳ ጋር ተመሳሳይ አጀማመር የነበራቸው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት አገግሞ በፉክክር ውስጥ መቆየትን ዘንድሮ በድጋሚ ለማሳየት የነገው ጨዋታ እጅግ አስፈላጊያቸው ነው። ቡድናቸው መሻሻሎችን ባሳየበት የባህር ዳሩ ጨዋታ የነበረውን ጠንካራ ጎን ማስቀጠል ደግሞ ዋነኛ አላማቸው ይመስላል።
ከአጨዋወት ምርጫ አንፃር የአርባምንጭ ከተማ ቀጥተኛ አቀራረብ ለሀዲያ ሆሳዕና የስጋት ነጥብ ይሆናል። በተለይም በባህር ዳሩ ጨዋታ በትኩረት ማነስ ባለቀ ሰዓት ግብ ያስተናገደው ቡድኑ መሰል ቀጥተኛ ኳሶች ወደ ሳጥኑ ሲደርሱ የሚያቋርጥበትን መንገድ ማጤን የግድ ይለዋል። አዞዎቹ በመልሶ ማጥቃት ከመስመሮች ወደ ግብ የሚደርሱበት ሁኔታም ለነብሮቹ የኋላ ክፍል ተጨማሪ የትኩሩት ነጥብ ነው። በሌላ በኩል ከኳስ ጋር ወደ ግብ መድረስ ላይ ጥሩ ሆነው የታዩት ሆሳዕናዎች የአጨራረስ ብቃታቸው ችግር በተደጋጋሚ ታይቷል።
የባዬ ፣ ሀብታሙ እና ዑመድን የቡድኑ የፊት መስመር ወረቀት ላይ አስፈሪ ቢመስልም የአጥቂዎቹ ውሳኔ አሰጣጥ መሻሻል በተለይም ከአማካይ ክፍሉ የመሀል ጥቃት በተጨማሪ እንደ ብርሀኑ በቀለ ዓይነት ተጫዋቾች ከመስመር የሚያደርሷቸውን ኳሶች ወደ ግብ የመቀየር የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የመሀል ሜዳ ተጫዋቾቻቸውን ወደ ግብ ማቅረብ እና የግብ ማግባት ሂደቱን ማገዝ ከሆሳዕናዎች የሚጠበቅ ነው።
በአርባምንጭ በኩል የፍቃዱ መኮንን እና አሸናፊ ተገኝ ጥምረት በመጨረሻው ጨዋታ በፈጠረው ተፅዕኖ በአሰልጣኙ ቀዳሚ አሰላለፍ ውስጥ ከተካተተ ዳግም የልዩነት ማዕከል ይሆናል ወይ የሚለው እጅግ ተጠባቂ ነው። የኬኒያዊው ኤሪክ ካፓይቶ ለጨዋታ ዝግጁ መሆንም የፊት መስመሩን ሞገስ ሊጨምረው ይችላል። ቡድኑ በታታሪነት ክፍተቶችን የመድፈን ብቃቱን አሻሽሎ መቅረብ እንዲሁም የመልሶ ማጥቃት አስፈሪነት ደረጃውን ጨምሮ መገኘት ይጠበቅበታል። በዚህ በኩል ከማጥቃት ሽግግሩ ፍጥነት በተጨማሪ ፊት ላይ የመጨረሻ ዕድሎች ሲገኙ በቁጥር ከተጋጣሚው የመከላከል ተሳታፊዎች ጋር በመመጣጠን አጋጣሚን ወደ ግብ የመቀየር ንፃሬውን ማሳደግ አስፈላጊው ነው።
በአርባምንጭ ከተማ ውስጥ የጉዳት ዜና የለም። ኤሪክ ካፓይቶ እና በርናንድ አቼንግ የወረቀት ጉዳዮች መጠናቀቅም ስብስቡን ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል። በሀዲያ ሆሳዕና በኩልም ሄኖክ አርፊጮ ከጉዳት መመለሱ መልካም ዜና ሲሆን አማካዩ ኤፍሬም ዘካሪያስ ግን የተጣለበትን ቅጣት አላገባደደም።
ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ፌደራል ዳኛ ሄኖክ አክሊሉ ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ያላቸው የእርስ በእርስ ግንኙነት በ2008 የውድድር ዓመት ብቻ ሲሆን አርባምንጭ አንዱን ጨዋታ 1-0 ሲያሸንፍ ሁለተኛው ጨዋታ በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አርባምንጭ ከተማ (4-3-3)
ሳምሶን አሰፋ
ወርቅይታደል አበበ – በርናንድ ኦቼንግ – ማርቲን ኦኮሮ – ተካልኝ ደጀኔ
እንዳልካቸው መስፍን – አንዱዓለም አስናቀ- አሸናፊ ተገኝ
በላይ ገዛኸኝ- ኤሪክ ካፓይቶ – ፍቃዱ መኮንን
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
መሳይ አያኖ
ብርሃኑ በቀለ – ፍሬዘር ካሳ – ኤሊያስ አታሮ – ሄኖክ አርፌጮ
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ተስፋዬ አለባቸው – ሳምሶን ጥላሁን
ዑመድ ዑኩሪ – ባዬ ገዛኸኝ – ሀብታሙ ታደሠ