ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የሶከር ኢትዮጵያ የሦስተኛ ሳምንት ምርጥ 11

ከቀናት በፊት የተቋጨው የዘንድሮው ውድድር ሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በመመርኮዝ ቀጣዩን ምርጥ ቡድን ሰርተናል።

አሰላለፍ – 3-4-1-2

ግብ ጠባቂ

መሐመድ ሙንታሪ – ሀዋሳ ከተማ

ከሁለተኛው ሳምንት በተቃረነ ሁኔታ ሦስተኛው ሳምንት የግብ ጠባቂዎች ምርጫ የተትረፈረፈ አልሆነም። በርካታ ሙከራዎችን አስተናግደው የተፈተኑ እና ውጤት ቀያሪ የሆነ ዕለት ያሳለፉ ግብ ጠጣቂዎች እንደልብ ባይገኙም የአዲስ አበባው ዳንኤል ተሾመ እና የሀዋሳው መሐመድ ሙንታሪ ሁለት ከቀድ ያሉ ኳሶችን ሲያድኑ ተመልክተናል። ከሙከራዎቹ ክብደት አንፃር ጋናዊው ግብ ጠባቂ የተሻለ ተመራጭ ሆኖ ስናገኘው ያዳናቸው ኳሶች 2-1 የተጠናቀቀውን ጨዋታ ውጤት ሙሉ ለሙሉ ሊቀይሩ ይችሉ ነበር።

ተከላካዮች

አስቻለው ታመነ – ፋሲል ከነማ

የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ቡድን ጅማ አባ ጅፋርን ሲገጥም ከሦስት ወደ አራት ተከላካዮች ተጠቃሚነት ተመልሷል። የቀኙን ወገን ይዞ ከያሬድ ባየህ ጋር የተጣመረው አስቻለው ታመነም ከቡድኑ ጋር በአግባቡ መዋሀድ መቻሉን ያሳየበት ሌላ የጨዋታ ቀን ብቃት አሳይቷል። ጅማ ፋሲልን በከባዱ ፈትኗል ባይባልም ከሌሎች ተከላካዮች ጋር ሲነፃፀር አስቻለው በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኘነቶች ወቅት የነበረው ትኩረት በሦስት ተከላካዮች በሚጀምረው የዚህ ሳምንት ምርጫችን ውስጥ እንዲካተት ምክንያት ሆኗል።

ፀጋሰው ድማሙ – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን በረታበት ጨዋታ እንደቡድን የነበረው የመከላከል አደረጃጀት ድንቅ ነበር። ከግቦቹ ባልተናነሰ አስተዋፅዖ በነበረው የመከላከል ሥራ ውስጥ ደግሞ ከነባሩ ላውረንስ ላርቴ ጋር በቶሎ የተዋሀደው አዲስ ፈራሚው ፀጋሰው ድማሙ ሚና የሚታይ ነበር። ከፍ ባለ ትኩረት ጨዋታውን የከወነው ተከላካዩ አደገኛ የአየር ላይ እና የመሬት ኳሶችን በማራቅ እንዲሁም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ጥሩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ የሲዳማ የፊት መስመር ፍሬ እንዳያፈራ አስታዋፅዖ ነበረው።

ኢያሱ ለገሰ – አዲስ አበባ ከተማ

የመዲናዋ ክለብ የዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥቦች ሲያሳካ የተከላካይ ክፍሉ ትኩረት ይልቅ ሚና ነበረው። በዚህ ውስጥ አምበሉ እያሱ ከልመንህ ታደሰ ጋር ጥሩ ጥምረት በማሳየት እና ቡድኑን በአግባቡ በመምራት ወሳኝ ሚና ተወጥቷል። ከሁሉም በላይ ግን ጨዋታው እንደተጀመረ የተቆጠረችው የፍፁም ጥላሁን ጎል መነሻ የነበረችውን ኳስ በረጅሙ ወደ አጥቂው ያደረሰበት መንገድ የጨዋታው ዋነኛ አበርክቶት ሆኖለታል። ግቧ በፍጥነት መቆጠሯ እና የኃይል ሚዛኑን መቀየሯ ደግሞ ኢያሱን ተስማሚ ተመራጭ ያደርገዋል።

አማካዮች

በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ

የታታሪነት ደረጃው እጅግ ከፍ ብሎ የውድድር ዓመቱን የጀመረው በረከት ፋሲል ጅማን በረታበት ጨዋታ የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋች የሚያስብለውን ብቃት አሳይቶናል። አራቱም ግቦች ላይ ተሳትፎ የነበረው በረከት የቡድኑ ዋና የማጥቃት ቀኝ እጅ ሆኖ ስንመለከተው ፍጥነቱ እና ቦታ አያያዙ ለጅማ ተጫዋቾች ፈተና ነበር። የመጀመሪያው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል እሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘ ሲሆን ሁለት ግቦች እንዲቆጠሩ ምክንያት የነበሩ የማጥቃት ሂደቶችን ሲያቀላጥፍ ቀሪውን አንድ ግብ ደግሞ አመቻችቷል። በሁለቱም መስመሮች የመንቀሳቀስ አቅሙን ከግምት ውስጥ በማስገባትም በመረጥነው የተጫዋቾች አደራደር የቀኝ ተመላላሽነት (wing-back)ን ሚና ሰጥተነዋል።

ሀብታሙ ተከስተ – ፋሲል ከነማ

ቁመተ ረጅሙ ቀጭን አማካይ ሌላኛውን ጠንካራ ጎኑን በሚገባ እያሳየን ይገኛል። ለሁለተኛ ጊዜ የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችን ውስጥ የተካተታው ሀብታሙ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ውስጥ ከኋላ ሆኖ ጥሩ ሽፋን ብበመስጠት እና ኳሶችን በማስጣሉ በኩል አሁንም በጥንካሬው እንደቀጠለ ነው። ከዚህ በተለየ በጅማው ጨዋታ ቡድኑ በነበረው ዕቅድ ውስጥ የከድር ኩሊባሊ ወደ አማካይ ክፍሉ መምጣት ሀብታሙን የማጥቃት ባህሪ እንዲላበስ አድርጎት ነበር። ይህንን በብቃት መወጣት የቻለው ተጫዋቹም በፋሲል አብዛኖቹ የማጥቃት ሂደቶች ውስጥ ክፍተቶችን አይቶ የጥቃት አቅጣጫዋችን በመወሰን ጉልህ ሚና ነበረው።

ቻርለስ ሪባኑ – አዲስ አበባ ከተማ

የመዲናዋ ቡድን በተከላካይ ፊት ባለው ቁልፍ ቦታ ላይ በመጀመሪያዎቹ ጨዋታዎች የተለያዩ አማራጮችን ሞክሯል። ከሥራ ፍቃድ ጋር በተያያዘ ጉዳዩ ያላላቀለት ናይጄሪያዊው አማካይ ወደ ተሰላፊነት መምጣት ግን እፎይ የሚያስብለው ይመስላል። ቻርለስ ሪባኑ በመከላከያው ጨዋታ ዋና ኃላፊነቱ የነበረውን ለተከላካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን የመስጠት የሥራ ድርሻ በአግባቡ ተወጥቷል። ወደ መስመር በማጋደል እንዲሁም መሀል ለመሀል የሚመጡ ጥቃቶችን በማቋረጥ አማካዩ የመከላከያዎችን ጥቃት ማርገብ መቻሉ ቡድኑ ላይ ሊፈጠር የሚችለውን ጫና በመቀነሱ በኩል ትልቅ አስተዋፅዖ ነበረው።

ያሬድ ሀሰን – አዲስ አበባ ከተማ

በግራ መሰር ተከላካይ ቦታ ላይ ከፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን ጋር የተፎካከረው ያሬድ ተመራጭ ሆኗል። ውድድሩን በአማካይነት ቢጀምርም በመከላከያው ጨዋታ በግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ የጀመረው ያሬድ የቡድኑ ጥቃት ያመዘነበተን የግራ ወገን ደጋግሞ ወደ ፊት በመሄድ ሲያግዝ ቆይቷል። በዚህም ሁለተኛው ግብ እንዲቆጠር ምክንያት የነበረው የቅጣት ምት እንዲገኝ ሲያደርግ ሦስተኛው ግብ የተቆጠረውም እርሱ ወደ ሳጥን ባደረሰው ኳስ መነሻነት ነበር። እኛም በግራ መሰር ተመላላሽነት የቡድናችን አካል አድርገነዋል።

በዛብህ መለዮ – ፋሲል ከነማ

ቡድኖች ከፊት አጥቂዎቻቸው በተጨማሪ አማካዮቻቸውም ግብ የማነፍነፍ ብቃት ሲኖራቸው እጅግ ዕድለኛ ይሆናሉ። በዚህ ረገድ ፋሲል ከነማ በዛብህ መለዮን አግኝቷል። ባለፈው ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ችሎ የነበረው በዛብህ በጅማው ጨዋታ ደግሞ ሁለት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ውስጥ የፈጠራ ምንጭ በመሆን ከፍ ያለ ድርሻን ሲወጣ የምንመለከተው ተጫዋቹ ዘግይቶ ሳጥን ውስጥ የሚደርስባቸው አጋጣሚዎች ከተከላካዮች እየታ እና ጫና ውጪ ሆኖ በጥሩ የአጨራረስ ብቃት ግቦችን እንዲያስቆጥር እያደረገው ይገኛል። ይህንን ከግምት በማስገባትም ከሁለት አጥቂዎች ጅርባ ያለውን ቦታ ሰጥተነዋል።

አጥቂዎች

ፍፁም ጥላሁን – አዲስ አበባ ከተማ

አዲስ አበባ ከተማ መከላከያን ሲገጥም ከሁለቱ የፊት አጥቂዎች አንዱ ሆኖ የተሰለፈው ፍፁም የጨዋታው ዋነኛ ልዩነት ፈጣሪ ሆኗል። ጨዋታው በተጀመረ 45 ሰከንዶች ውስጥ ከመረብ ያገናኘው ኳስ አጠቃላይ የፉክክሩን መንፈስ ቀይሯል። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎችም የቡድኑ ዋና የጥቃት መሳሪያ ሆኖ የተመለከትነው ፍፁም በዚህም ጨዋታ የስጋት ምንጭ ሆኖ ቆይቶ የአዲስ አበባን አሸናፊነት ያረጋገጠችውን ሦስተኛ ግብም በስሙ አስመዝግቧል።

ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ

ወጣቱ የሀዋሳ ከተማ አጥቂ ዘንድሮ ከአምናው የተሻለ አቋም ላይ እንደሚገኝ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ፍንጭ ሰጥቶ ነበር። በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ላይ በተጠበቀው መልኩ ባይንቀሳቀስም በሲዳማው ጨዋታ ከቡድን ጓደኞቹ ጋር በታታሪነት የተሞላ አመርቂ ዘጠና ደቂቃ አሳልፏል። ቡድኑ ቀዳሚውን ጎል ሲያስቆጥር የተከላካዮችን አቋቋም በማሳት እና ኳሱን ከመሀል ማዳ ሳጥን ድረስ በመግፋት ተሳትፎ ሲያደርግ ወሳኝ የነበረችውን የማሸነፊያዋን ግብ ደግሞ ራሱ አስቆጥሯል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

በሳምንቱ በሰፊ ግብ ልዩነት ድል ያጣጣሙት አሰልጣኝ ስዩም ከበደ እና አሰልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ጋር ለኮከብነት የተፎካከሩት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቅድሚያውን መውሰድ ችለዋል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ከሲዳማ ቡና ጋር የነራቸው ጨዋታ የደርቢ ፉክክር ከመሆኑም ባለፈ ሲዳማ ቡና ጠንካራ አቋም ላይ ይገኝ የነበረ በመሆኑ ነው። የአሰልጣኙ የጨዋታ ዕቅድም የሲዳማን ጠንካራ የማጥቃት ጎኖች በማክሸፉ በኩል ስኬታማ የነበረ ሲሆን በማጥቃቱም ረገድ የቡድኑ አስፈሪ ፈጣን ጥቃት ሁለት ግቦችን ሊያስገኝለት ችሏል።

ተጠባባቂዎች

ዳንኤል ተሾመ – አዲስ አበባ ከተማ
ልመንህ ታደሰ – አዲስ አበባ ከተማ
አምሳሉ ጥላሁን – ፋሲል ከነማ
አዉዱ ናፊዩ – ድሬዳዋ ከተማ
አብዱለጢፍ መሐመድ – ድሬዳዋ ከተማ
አብዱልባሲጥ ከማል – ሀዋሳ ከተማ
ኤፍሬም አሻሞ – ሀዋሳ ከተማ
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ