ኢትዮጵያን ከ31 አመታት በኃላ ወደ አፍሪካ መድረክ የመለሱት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስንብት ከተሰማ በኃላ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡
በአሰልጣኙ ቆይታ ቁልፍ አጥቂ ሆኖ ያገለገለው ሳላዲን ሰኢድ ‹‹ የመባረራቸውን ዜና አሁን መስማቴ ነው ፤ ውሳኔው አስደንጋጭ ነው፡፡ ቢሆንም ለቀጣይ የብሄራዊ ቡድኑ እድገት ስም ያለው አሰልጣኝ ከአውሮፓ ቢመጣ ጥሩ ነው›› ሲል ለሱፐር ስፖርት ተናግሯል፡፡
የአህሊ ሼንዲው አማካይ አዲስ ህንፃ ከኢትዮ ኪክ ኦፍ ጋር ባደረገው ቆይታ ‹‹ ሰውነት ለኛ ጥሩ ነበሩ ፤ ህብረት እና ተነሳሽነትን በቡድናችን ውስጥ አምጥተዋል፡፡››
‹‹ የውጭ ዜጋ በአሰልጣኝነት ከተሾመ የሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እየተቃረበ እንደመምጣቱ ቡድኑን ለመላመድ እና በቶሎ ውጤታማ ለመሆኑ ጥርጣሬ አለኝ›› ሲል ተናግሯል፡፡
የቅዱስ ጊዮርጊሱ የመስመር አማካይ በኃይሉ አሰፋም የአሰጣኙን ስንብት ኮንኗል፡፡ ‹‹ ፌዴሬሽኑ ትልቅ ስህተት ሰርቷል፡፡ አሰልጣኙ ለብሄራዊ ቡድናችን ትክክለኛው ሰው ነበሩ፡፡ የትኛውም አሰልጣኝ ቢመጣ የሁሉን ተጫዋቾች ባህርይ ተከትሎ የሚሰራ የለም.. ሲል ለኢትዮ ከሊክ ኦፍ ገልጧል፡፡