ኢትዮጵያ ቡናን በዚህ የውድድር ዘመን ማገልገል ያልቻሉት ሦስት ተጫዋቾች ከጉዳታቸው አገግመዋል።
ለረጅም ወራት ከሜዳ የራቀው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ተመስገን ካስትሮ ልምምድ ጀምሯል። ከአርባምንጭ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመጣ በኃላ የእግርኳስ ህይወቱን ጉዳት እየተፈታተነው የሚገኘው ሁለገቡ ተመስገን ለረጅም ወራት ጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ከሜዳ በመራቁ ወደ ህንድ በማቅናት የተሳካ ህክምና አድርጎ መመለሱ ይታወሳል።
አሁን ከጉዳቱ ያገገመው ተመስገን ከቡድኑ ጋር በመቀላቀል ቀለል ያሉ ልምምዶችን መጀመሩ ሲታወቅ በቅርቡ ወደ ጨዋታ ሊመለስ እንደሚችል ሰምተናል። ለረጅም ጊዜ ከሜዳ በመራቁ በጣም ፈታኝ ጊዜ እንዳሳለፈ የሚናገረው ተመስገን “በአካልም በስነ ልቦናውም በሚገባ ተዘጋጅቼ ኢትዮጵያ ቡናን ለማገልገል አስባለው” ብሏል።
ከተመስገን በተጨማሪ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ክለቡን የተቀላቀለው ተከላካዩ ነስረዲን ኃይሉም ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ መጀመሩን ክለቡ የገለፀ ሲሆን የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሬድዋን ናስርም ከጉዳቱ በማገገሙ በቅርቡ ልምምድ እንደሚጀምር ይጠበቃል።