በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሦስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ የዲሲፕሊን ጥሰት በፈፀሙ ተጫዋቾች እና ሌሎች አካላት ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላልፏል፡፡
የ2014 ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በሚል ሊጉ ከቀናቶች መቋረጥ በኋላ የፊታችን ኅዳር 12 በአራተኛ ሳምንት መርሐግብሮች ይቀጥላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ በሦስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ የታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ ውሳኔውን በተጫዋቾች እና ሌሎች አካሎች ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
የፋሲል ከነማ ተጫዋች የሆነው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ክለቡ ፋሲል ከነማ ጅማ አባ ጅፋር ሲያሸንፍ በ84ኛ ደቂቃ ላይ ተጫዋቹ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን ሲገልፅ በውስጥ ልብሱ ላይ ሃይማኖታዊ መልዕክት የሚያስተላልፍ ምስል ስለ ማሳየቱ ሪፖርት ቀርቦበታል። ስለሆነም የቡድኑ ተጫዋች ለፈፀመው ጥፋት ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ብር 3000 ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ ተጫዋች የሆነው ፍፁም ጥላሁን ክለቡ መከላከያን 3ለ0 ሲያሸንፍ በ61ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ካገባ በኋላ ተጫዋቹ ደስታውን ሲገልፅ በውስጥ ልብሱ ላይ ሃይማኖታዊ መልዕክት የሚያስተላልፍ ምስል ስለ ማሳየቱ ሪፖርት ቀርቦበታል ። ስለሆነም የቡድኑ ተጫዋች ለፈፀመው ጥፋት ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት 3000 ብር እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
መከላከያ በአዲስ አበባ ከተማ 3ለ0 ሲሸነፍ በ87ኛው ደቂቃ ላይ በሁለት ቢጫ የቀይ ካርድ ተመልክቶ የነበረው ገናናው ረጋሳ 1 ጨዋታ እንዲታገድ ሲወሰን ሀድያ ሆሳዕና ከአርባምንጭ ከተማ ጋር 1ለ1 ሲለያይ በ82ኛው ደቂቃ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ የተወገደው አማካዩ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንም በተመሳሳይ የአንድ ጨዋታ እገዳ ተላልፎበታል፡፡
ሀዋሳ ከተማ ሲዳማ ቡናን 2ለ1 ሲረታ የሀዋሳ ከተማው ስራ አስኪያጅ አቶ ኡቴሳ ኡጋሞ እና የሲዳማ ቡናው የቦርድ አባል አቶ አዲሱ ቃሚሶ በወቅቱ በጨዋታው ላይ ወደ መጫወቻ ሜዳው ላይ የፕላስቲክ ጠርሙስ በመወርወራቸው ሁለቱም እያንዳንዳቸው የ25 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡