በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና በከፍተኛ ሊግ ለሚገኙ ክለቦች ትጥቆችን በማቅረብ ራሱን ወደ ገበያው እያስገባ የሚገኘው ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ጎፈሬ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አብሮ ለመስራት ቅድመ ስምምነት በዛሬው ዕለት አድርጓል።
በቅድመ ስምምነቱ ላይ በጎፈሬ የትጥቅ ማምረቻ በኩል አቶ አቤል ወንድወሰን ሲገኙ አዲስ አበባ ከተማን በመወከል የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ታከለ ተገኝተዋል። በቅድምያ ጎፍሬ ለቡድኑ 32 ተጫዋቾች እና የአሰልጣኞች አባላት የመጫወቻ መለያ በማበርከት ቅድመ ስምምነቱን ያበሰረ ሲሆን በቀጣይ ሰፋ ባሉ ጉዳዮች ላይ አብረው እንደሚሰሩ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ታከለ የጎፈሬን ትጥቅ ማምረቻ ስፍራን ከጎበኙ በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
” ዛሬ የጎፈሬ ትጥቅ ማምረቻን እንደጎበኘነው ከሆነ በጣም የተደመምንበት ሁኔታ ነው ያለው። የሀገራችንን ምርት የማበረታታት የመደገፍ ኃላፊነት አለበን። በዚህ ውስጥ ደግሞ የስራ አጥ ቁጥር በመቅረፍ አብዛኛው ሴት እህቶቻችን በሥራው ተሰማርተው ማግኘታችን በጣም ነው ደስ ያሰኛል። የሀገር ምርትም ስታበረታታ ሀገር እያደገች የውጭ ምንዛሪ እያስቀረን ለትጥቅ ብለን የምናወጣውን ከፍተኛ ወጪ የሚቀንስልን ይሆናል። እንዲሁም ከዚህ ቀደም ከውጭ በሚመጡ መለያዎች የሚያጋጥመን ከመጠን ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮን በሚገባ የሚቀርፍ ስለሆነ ከዚህ ተቋም ጋር አብሮ መሥራት እንዳለብን ያስገነዝባል። በዛሬው ዕለትም የተጫዋቾቻችን ስማቸው የታተመበት መጫወቻ መለያ ለአሰልጣኞች አባላትም ደረጃውን የጠበቀ ትጥቅ ድጋፍ ተደርጎልናል። በዚህም በጣም እያመሰገንን እንደ አዲስ አበባ እግርኳስ ክለብ በቀጣይ በሴቱም በወንዱም ቡድኖች እንዲሁም በደጋፊዎች መለያ ወደፊት በምናደርጋቸው የገቢ መሳባሰቢያ ሩጫዎች ወዘተ ከጎፈሬ ጋር አብረን ለመስራት የምንፈራረም መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ አረጋግጣለሁ። ይሄንን ሀሳባችንን ከጎናችን ሆኖ በመደገፍ በማገዝ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን እንዲሁም የከንቲባ ቢሮ ከጎናችን በመሆናቸው በዚህ አጋጣሚ እናመሰግናለን።”
በነገው ዕለት በአራተኛ ሳምንት አዲስ አበባ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ በጎፈሬ የተመረተውን አዲሱን መለያ በመልበስ ወደ ሜዳ የሚገባ ይሆናል።
ጎፈሬ ከዚህ ቀደም ከከፍተኛ ሊግ አንድ ከፕሪምየር ሊግ ከስድስት ክለቦች ጋር በይፋ አብሮ እየሰራ ሲሆን ከባህር ዳር ከተማ እና ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አብሮ ለመስራት ቅድመ ስምምነቶችን በማድረግ ወደ ትግበራ እንደገባ ሲታወቅ በቅርቡ ይፋዊ ስምምነት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።