አራት ግቦች በተስተናገዱበት የአራተኛ ሳምንት አምስተኛ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ ቡናን 3-1 አሸንፏል።
ከተከታታይ ሁለት ድል በኋላ ዛሬ ለጨዋታ የቀረቡት ወላይታ ድቻዎች ከመጨረሻው ጨዋታቸው በቤተሰብ ሀዘን ምክንያት ፍቃድ የተሰጠው አንተነህ ጉግሳን ብቻ በቃልኪዳን ዘላለም ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። የመጀመሪያ ድላቸውን ለማግኘት ስታዲየም የደረሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ አራት ለውጦችን በማድረግ ጨዋታውን ጀምረዋል። በዚህም ሥዩም ተስፋዬ፣ ዊልያም ሰለሞን፣ ወንድሜነህ ደረጄ እና አላዛር ሺመልስ ኃይሌ ገብረትንሳይ፣ ቴዎድሮስ በቀለ፣ ሮቤል ተክለሚካኤል እና አቤል እንዳለን ተክተው እንዲጫወቱ ተደርጓል።
ኳስን በተሻለ በመቆጣጠር ጨዋታቸውን ማድረግ የጀመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአመዛኙ ወደ ግራ መስመር (አቡበከር እነና አስራት በተሰለፉበት) በማጋደል ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሲጥሩ ነበር። ኳሱን ለቡና ሰተው በወሳኝ አጋጣሚዎች ላይ ብቻ ፍጥነትን በመጠቀም መጫወት የመረጡት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል አምርተው ሳያፍሩ ተመልሰዋል። በዚህም በ11ኛው ደቂቃ ቃልኪዳን ዘላለም ምንይሉ ወንድሙ ከመዓዘን ያሻገረውን ኳስ በሩቁ ቋሚ የነበረው በረከት ወልደዮሐንስ በግንባሩ ሲያቀብለው በቀጥታ አቤል መረብ ላይ አሳርፎት ቡድኑን መሪ አድርጓል።
አሁንም ከኳስ ጋር የሚያሳልፉትን ጊዜ ጨመር አድርገው ሲጫወቱ የታዩት ቡናማዎቹ በ18ኛው ደቂቃ አላዛር ሺመልስ ከእንዳለ ደባልቄ ተቀብሎ ወደ ግብ በመታው ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር። ግን ተጫዋቹ በተከላካይ መሐል ያገኘውን ኳስ እንዳይጠቀም አናጋው ባደግ ደርሶ አውጥቶታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በተመሳሳይ ድንቅ የተከላካይ የመከላከል እንቅስቃሴ በተቃራኒ ቡድን ተመልክተናል። በዚህም ስንታየሁ መንግስቱ ከረጅም ርቀት የተላከለትን ኳስ ቁመናውን ተጠቅሞ ወንድሜነህ ደረጄን አልፎ ሳጥን ውስጥ በመግባት ወደ ግብ የመታውን ጥሩ ኳስ አበበ ጥላሁን እንደምንም ጨርፎ አውጥቶታል።
እየተሟሟቀ የሄደው ጨዋታው በ25ኛው ደቂቃ ደግሞ ሌላ ያለቀለት የግብ ዕድል አስተናግዷል። በተጠቀሰው ደቂቃም እንዳለ ደባልቄ ለአቡበከር ናስር ያሻማውን ኳስ አቡበከር በግንባሩ ወደ ግብ ቢመታውም የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ፅዮን መርዕድ እና የግቡ አግዳሚ ተጋግዘው ኳሱን ከግብነት ታድገውታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ አስራት ቱንጆ ከመስመር ሰብሮ በመግባት ከርቀት የከረረ ኳስ መቶ ለጥቂት ወጥቶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ቡድኑ በአቡበከር እና አላዛር አማካኝነት ሌሎች ሙከራዎችን ቢያደርግም አቻ የመሆን ውጥኑ ሳይሰምር አጋማሹ ተገባዷል።
የሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ትንቅንቅ በማስተናገድ ገና ከጅምሩ ግቦችን ማስመልከት ይዟል። በቅድሚያም ወላይታ ድቻ መሪነቱን ያሰፋበትን ጎል አግኝቷል። በዚህም በ49ኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር ጥፋት ሰርቶ የተገኘውን የቅጣት ምት አናጋው ባደግ ሲያሻማው ምንይሉ ወንድሙ ለስንታየሁ አመቻችቶለት ቁመታሙ አጥቂ ኳስ እና መረብን በግራ እግሩ አገናኝቷል። ፈጣን ምላሽ ለመስጠን ያላመነቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ግብ አግኝተዋል። በዚህም ታፈሰ ሰለሞን በግራ መስመር ከነበረው አቡበከር ናስር የተቀበለውን ኳስ ፅዮን መረብ ላይ አሳርፎታል። ይህ ግብ ያነቃቃው ቡድኑም በ56ኛው ደቂቃ በእንዳለ አማካኝነት ሌላ ሙከራ አድርጎ ነበር።
ጨዋታው 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ደግሞ አራተኛ ግብ ተቆጥሯል። በዚህም በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፈው ላለመስጠት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ሲጫወቱ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በረጅሙ ወደ ቡና የላኩት ኳስ መሪነታቸውን አስፍቶላቸዋል። በዚህም ከርቀት የተመታውን ኳስ ከአራት ደቂቃዎች በፊት የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው ቃልኪዳንን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ቢኒያም ፍቅሬ ለስንታየሁ አመቻችቶለት ስንታየሁ ከሳጥን ውጪ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል።
ብዙ ነገሮች ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነባቸው የመጣው የአሠልጣኝ ካሳዬ አራጌ ተጫዋቾች በ71ኛው ደቂቃ ታፈሰ አሻምቶግ አቡበከር በግንባሩ ለማስቆጠር በሞከረው የቅጣት ምት ሁለተኛ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ የግብ ጠባቂው ፅዮንን ከመዘናጋት የመጣ ስህተት ተከትሎ አቡበከር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ለያብቃል ቢሰጠውም የመስመር አጥቂው አጨራረሱን ሳያሳምር ቀርቶ ኳሱን አምክኖታል። ሮቤል ተክለሚካኤልም የዕለቱ ዳኛ ፊሽካ ሊነፉ ሲል አክርሮ መቶ ፅዮን አድኖበታል። በቀሪ የጨዋታው ደቂቃዎች ሌላ ግብ ሳይስተናገድ ወላይታ ድቻ ሦስት ነጥብ አግኝቶ ከሜዳው ወጥቷል።
ውጤቱን ተከትሎ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ያገኙት ወላይታ ድቻዎች ነጥባቸውን ዘጠኝ በማድረስ ከመሪው ፋሲል ጋር በመስተካከል በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጠው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። እስከ አሁን አንድም ጨዋታ ያላሸነፉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ በሁለት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።