የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የአራተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን በሚከተለው መልኩ ቃኝተነዋል።
ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት በሀዋሳ ከተማ ተረተው የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ዳግም ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመምጣት እና ደረጃቸውን ለማሻሻል ጠንክረው ለነገው ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይታሰባል።
በአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ቡድኑ በሀዋሳ ከመሸነፉ በፊት በነበሩት ሁለት ጨዋታዎች (ከኢትዮጵያ ቡና እና ከድሬዳዋ ከተማ) በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ጠንካራ እንደሆነ አሳይቷል። በተለይ ፍጥነት የታከለበት ሽግግሮችን በማድረግ ተጋጣሚን ለማስጨነቅ ሲጥር የተስተዋለ ሲሆን ይህ ጠንካራ ጎኑ ግን በሀዋሳው ጨዋታ ቀዝቀዝ ብሎ ታይቷል። ያለፉትን ቀናት ሊጉ ተቋርጦ የነበረ መሆኑ ደግሞ መቀዛቀዝ ያሳየውን የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ አሠልጣኙ እንዲያሻሽሉ ጊዜ የሚሰጥ ይሆናል። ከምንም በላይ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እንደሚቸገር ፍንጭ የታየበትን ክፍተት አሻሽለው ነገ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይገመታል።
በተለያዩ የጨዋታ ሂደቶች የግብ ዕድሎችን መፍጠር የሚችለው ሲዳማ እንደሚፈጥራቸው አጋጣሚዎች ግቦችን ሲያስቆጥር አይታይም። ይህ የጎል ፊት አይናፋርነት ነገም ከቀጠለ ደግሞ በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት ተጋጣሚው ሰበታ እምብዛም ላይፈተን ይችላል። ከምንም በላይ ግን በአጥቂ አማካይ ቦታ የሚሰለፈው ፍሬው እንዲሁም ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ሰለሞን እና አማኑኤል በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል እየተገኙ የሚፈጥሯቸው ዕድሎች ነገም ዋጋቸው ከፍተኛ ነው።
እስካሁን አንድም ጨዋታ ያላሸነፉት ሰበታዎች የዓመቱ የመጀመሪያ ድላቸውን በሁለት ነጥብ እና ደረጃ የሚበልጧቸው ሲዳማዎች ላይ ለማግኘት ተግተው ጨዋታውን እንደሚቀርቡ ይታመናል።
በእስካሁኖቹ የሊጉ ጨዋታዎች ዝቅተኛ ግብ (1) ያስተናገደው ሰበታ ጠንካራ የመከላከል አጨዋወቱ ለተጋጣሚ ቡድኖች ፈተና እየሆነ ነው። በተለይ በቁመትም ሆነ በስፋት ችምችም ብሎ በመጫወት ተጋጣሚ ተጫዋቾች የግብ ዕድሎችን እንዳይፈጥር የሚያደርግበት መንገድ የሚደነቅ ነው። ይህ ቡድናዊ መዋቅር ደግሞ ነገ በፈጣኖቹ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል። ከዚህ ውጪ ኳስን ለሲዳማ ሰጥቶ ሽግግሮች ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት አጨዋወት በቡድኑ በኩል እንደሚኖር ይጠበቃል።
ብቸኛው ኳስ እና መረብን ያላገናኘ ክለብ የሆነው የአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን የማጥቃት ሀይሉን በነበረው የእረፍት ጊዜ አሻሽሎ መምጣት የግድ ይለዋል። እርግጥ በሦስቱ ጨዋታዎች ቡድኑ በአብዛኛው ቀጥተኛ እና የመልሶ ማጥቃት አጨዋወትን ሲከተል ቢታይም የሰላ የመሆን ክፍተት ይስተዋልበታል። ይህ የስልነት ችግር ከተሻሻለ ግን በስብስቡ ውስጥ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ስላሉ ሲዳማዎች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። ሌላው ሲዳማ ቡና በሀዋሳ ሲረታ በመስመር በኩል ለማጥቃት ጥሮ መስመሮች ሲዘጉበት የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገር ስለታየ ሰበታም በተመሳሳይ የመከላከል አደረጃጀት ጨዋታውን ሊቀርቡ ይችላል።
በሲዳማ በኩል ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን ሰበታ ግን ወሳኝ ተጫዋቾችን ጨምሮ በድምሩ አምስት ተጫዋቾችን በነገው ጨዋታ አያገኝም። በዚህም በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ቀይ ካርድ ያየው አንተነህ ተስፋዬን ጨምሮ ጌቱ ሀይለማርያም፣ መሀመድ አበራ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና ዱሬሳ ሹቢሳ ነገ በጉዳት ምክንያት አይኖሩም።
ይህንን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ ኢያሱ ፈንቴ በአልቢትርበት የሚመሩት ይሆናል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ ነገ ሰባተኛ የሊግ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። በእስካሁኖቹ ስድስት ግንኙነቶችም ሲዳማ ቡና አራቱን በድል ሲያጠናቅቅ ሰበታ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል። አምና በሁለተኛው ዙር ያለ ግብ የተጠናቀቀው ጨዋታ ብቸኛው የአቻ ውጤታቸው ሆኗል።
– በጨዋታዎቹ ሲዳማ አምስት ግቦች ሲኖሩት ሰበታ ሁለት ግቦችን አስመዝግቧል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ለዓለም ብርሀኑ
ታፈሰ ሰርካ – በረከት ሳሙኤል – ወልደአማኑኤል ጌቱ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
በሃይሉ ግርማ – ክሪዚስቶም ንታንቢ
ፍፁም ገብረማርያም – ሳሙኤል ሳሊሶ – ዘካሪያስ ፍቅሬ
ጁኒያስ ናንጄቤ
ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)
ተክለማሪያም ሻንቆ
አማኑኤል እንዳለ – ጊትጋት ጉት – ያኩቡ መሀመድ – ሰለሞን ሀብቴ
ብርሀኑ አሻሞ – ቴዎድሮስ ታፈሰ
ብሩክ ሙሉጌታ – ፍሬው ሰለሞን – ፍራኒሲስ ካሀታ
ይገዙ ቦጋለ