ውል እያለው ተሰናብቶ በነበረው የግራ መስመር ተከላካይን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ የወሰነው ውሳኔን ተግባራዊ ባላደረገው ወላይታ ድቻ ላይ የመጨረሻ ውሳኔውን አሳልፏል፡፡
ወላይታ ድቻን በሁለት ዓመት ውል 2012 ላይ ተቀላቅሎ የነበረው ይግረማቸው ተስፋዬን በዛው ዓመት አጋማሽ ላይ ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡ ተጫዋቹም በወቅቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረበው አቤቱታ መሠረት ከረጅም ጊዜያት ሂደት በኋላ ፌዴሬሽኑ ወላይታ ድቻ ተጫዋቹን ወደ ስራ ገበታው እንዲመልስ እና ለተጫዋቾቹም ያልተከፈለው ገንዘብ ተፈፃሚ እንዲሆን በላከው ደብዳቤ መግለፁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ክለቡም ለፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ ይግባኝ ቢልም በዲሲፕሊን ኮሚቴው በተደጋጋሚ ውድቅ ሲሆንበት የተስተዋለ ሲሆን አሁንም ድረስ ክለቡ የተወሰነበትን ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረጉ ተጫዋቹ ውሳኔው ተፈፃሚ እንዳልሆነለት ቅሬታን በማሰማቱ የመጨረሻ ውሳኔ በወላይታ ድቻ ላይ አሳልፏል፡፡
በህግ ጠበቃው ብርሀኑ በጋሻው አማካኝነት ጉዳዩን ሲከታተል ለነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ፌድሬሽኑ ክለቡ የተወሰነውን ውሳኔ ተግባራዊ ባለማድረጉ ከቀጣዩ የተጫዋቾች ዝውውር ጀምሮ ክለቡ የታገደ መሆኑን በደብዳቤ በመግለፅ ከፌዴሬሽኑም አገልግሎት እንዳያገኝ ውሳኔን በክለቡ ላይ አስተላልፏል፡፡