በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጋራ ጥምረት የካፍ ዲ ላይሰንስ የአሰልጣኞች ስልጠና በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡
ከአመታት በኋላ ከተቋረጠበት የጀመረው የካፍ የአሰልጣኞች ስልጠና በያዝነው አመት በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሰጠት የጀመረ ሲሆን የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበርም አዲስ ባመጣው የዲ ላይሰንስ የስልጠና ሂደት መሠረትን በሀገራችን ኢትዮጵያ መሰጠት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል፡፡ በባህርዳር ፣ በአዲስ አበባ እና አዳማ ከተማ በድምሩ ዘጠና ለሚጠጉ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ሲሰጥ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ አራተኛው ዙር የዲ ላይሰንስ ስልጠና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በጋራ በመሆን ማለትም ከዛሬ ህዳር 23 ጀምሮ ለተከታታይ አስራ አንድ ቀናት የሚቆይ ስልጠና በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል መሰጠት ጀምሯል፡፡
በካፍ አዲሱ አሰራር መሠረት በአንድ የስልጠና ሂደት ሰላሳ ሰልጣኞችን አቅፎ የሚሰጠው ስልጠና በዛሬው ዕለት በይፋ ጅምሩን ሲያደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር ተወካይ እና የኢንስትራክተሮች ፣ የአሰልጣኞች ትምህርት ክፍል ሀላፊ አቶ ደረሰ እሸቱ ፣ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ እንዲሁም የካፍ ኤሊት ኢንስራክተር አብረሀም መብራቱ ፣ ይህንን ስልጠና በዋና የሚሰጡት እና ዳይሬክተሩ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገብረማርያም እና እንስቷ ኢንስትራክተር በሀይሏ ዘለቀ ተገኝተው ይህንን ስልጠና በጋራ አስጀምረዋል፡፡
አቶ አንበሴ አበበ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “በእነኚህ ኢንስትራክተሮች ለመሰልጠን በመምጣታችሁ ዕድለኞች ናችሁ ወደፊት በተሻለ ብቃት እንድትገኙ ይህ ስልጠና ስለሚያስፈልጋችሁ ጠንክራችሁ ሰልጥነሠችሁ ለክልላችንም ሆነ ለሀገራችን መልካም ስራ እንድትሰሩ ምኞቴ ነው፡፡ ስልጠናውንም በተግባር ልታሳዩን ይገባል ለተተኪ ስፖርተኞች መሰረት በመሆናችሁ ትኩረት በመስጠት የሚሰጣችሁን ተከታትላችሁ እንደምታኮሩን እምነቴ ነው። የክልሉ እግር ኳስ ፌድሬሽን ሁሌም በማንኛውም ሰአት ከጎናችሁ እንደሆንን ለመናገር እፈልጋለሁ።” ሲሉ በመክፈቻ ንግግራቸው ገለፃ ካደረጉ በኋላ አቶ ደረሰ እሸቱ በስልጠናው ሰልጣኞች ሊያደርጉ ስለሚኖርባቸው መመሪያዎች ያብራሩ ሲሆን በመቀጠልም ስልጠናውን በዋናነት የሚሰጡት ኢንስራክተሮች ንግግር አድርገዋል፡፡ ዕድሜያቸው ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ያሉ ታዳጊ ተጫዋቾች በተመለከተ በስፋቶ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰጠውን የካ ዲ ላይሰንስ ስልጠናን በዋናነትነት የካፍ ኢንስራክተር ዳንኤል ገብረማርያም በዋናነት በአሰልጣኝነት የሚመሩት ሲሆን ኢንስትራክተር በሀይሏ ዘለቀ እና ኢንስራክተር ሰላም ዘርአይ እንዲሁም ሌሎች አሰልጣኞች በተጋባዥነት በመገኘት ስልጠናውን እንደሚሰጡ ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ ተገንዝባለች፡፡
የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብረሀም መብራቱ በመጨረሻ ንግግራቸው የተለያዩ ሀሳቦችን ስለ ስልጠናው እና መሰል ሂደቶች ለሰልጣኞች ካብራሩ በኋላ ስልጠናው በይፋ ለስልሳ ሰአታት እንደሚሰጥ ተገልፆ ጅምሩን አድርጓል፡፡ በክፍል እና በተግባርም ስልጠናው እንደሚሰጥም ተነግሯል፡፡