የስድስተኛ ሳምንት የመክፈቻ ቀን ሁለተኛ ጨዋታን በሚከተለው መልኩ ቃኝተነዋል።
እስካሁን 15 ነጥቦች በሚገኝባቸው አምስት ጨዋታዎች አንድም ድል ያላደረገው ሀዲያ ሆሳዕና ከድል ጋር ታርቆ ከመጥፎ አጀማመሩ ለመላቀቅ በወቅታዊ ብቃት ጥሩ የሆነውን አዲስ አበባ ከተማን ይገጥማል።
በእንቅስቃሴ ደረጃ ለክፉ የሚሰጥ ነገር በአምስቱ ጨዋታዎች ያላሳየው ሀዲያ ነገሮችን ከፍጥነት ጋር አለማድረጉ ዋጋ እያስከፈለው ይመስላል። በተለይ ደግሞ በማጥቃቱ ረገድ ፍጥነት አልባ ስልት መከተሉ የተጋጣሚ ተከላካዮች ብዙም እንዳይረበሹ ያደረገ ይመስላል። እርግጥ በቡድኑ ውስጥ ፍጥነት ያላቸው ተጫዋቾች በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ቢኖሩም መዋቅራዊው የማጥቃት አጨዋወት ግን ዝግ ያለ ነው። ምናልባት ይህ ጉዳይ በነገው ጨዋታ ተቀርፎ ከመጣ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ካስቆጠረው ጅማ እኩል የሆነው የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ቡድን አዎንታዊ ነገር ሜዳ ላይ ሊገጥመው ይችላል።
ከመጥፎው የሊጉ አጀማመር ማግስት ጠንክሮ የታየው አዲስ አበባ ከተማ ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በአልቀመስ ባይነቱ ቀጥሏል። ነገም ድል ከናፈቀው ሀዲያ ጋር በመፋለም የደረጃ ሰንጠረዡን አጋማሽ በመልቀቅ ወደ ላይ መውጣትን አልሞ ጨዋታውን ይጀምራል።
አዲሱ የሊጉ ክለብ አዲስ አበባ በሲቲ ካፕ እና በሊጉ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታዎች ባሳየው ብቃት ብዙዎች ትንሽ ቦታ ቢሰጡትም በምክትል አሠልጣኙ ደምሰው እየተመራ እጅን አፍ ላይ የሚያመጣ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። ያለ ብዙ የተጫዋቾች ምርጫ ለውጥ እና ጥልቀት ያላቸው ታክቲካዊ ጉዳዮች በላይ ቡድኑ እንደ አዲስ ያመጣው ያልሸነፍ ባይነት ባህሪ ከሁሉም በላይ ቦታ የሚይዝ ይመስላል። በአምስተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታም ባለቀ ሰዓት ግብ ተቆጥሮበት ነጥብ ጣለ እንጂ ሦስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማግኘት ከጫፍ ደርሶ ነበር። በጨዋታዎቹ ላይ ደግሞ በሁሉም የጨዋታ ሂደቶች የሚታዩት ቡድናዊ እንቅስቃሴዎች ውጤት እያስገኘለት እንደሆነ በጉልህ ተስተውሏል። ነገም ይህ ባህሪ ከተደገመ ሀዲያ ፈተና እንደሚበዛበት ይገመታል።
በነገው ጨዋታ አማካይ መስመር ላይ የሚኖረው ፍጥጫ ትኩረትን የሚስብ ይሆናል። እርግጥ ሀዲያ በአንፃራዊነት ኳስን ለመቆጣጠር ፍላጎት እንደሚኖረው ቢገመትም በጥሩ መነቃቃት ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ኳሶችን እያቋረጠ በፍጥነት ወደ ግብነት ለመቀየር የሚጥርበት መንገድ በጨዋታው ሊታይ የሚችል ጉዳይ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ በኩል ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ጥሩ የነበረው ኤሌያስ አህመድ ሲጠበቅ በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ደግሞ የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ዑመድ ኡኩሩ የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ።
ሀድያ ሆሳዕና ኤፍሬም ዘካሪያስን ከቅጣት ሄኖክ አርፊጮ እና መሳይ አያኖን ከጉዳት መልስ ሲያገኝ ባዬ ገዛኸኝ ግን በጉዳት ሁለተኛ ተከታታይ ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል። አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ አሁንም የቴዎድሮስ ሀሞ፣ ፈይሰል ሙዘሚል እና ነብዩ ዱላን ግልጋሎግ አያገኝም። አሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር ከተነሱ በኋላ ቡድኑን ለሦስት ጨዋታዎች በጊዜያዊነት እንዲመሩ ሀላፊነት የተሰጣቸው ምክትል አሠልጣኙ ደምሰው ፍቃዱም አሁንም በመንበራቸው እንዲቀጥሉ በመደረጉ ነገ ቡድኑን እንደሚመሩት ተመላክቷል።
ሁለቱ ክለቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ከፍተኛው የሊግ እርከን እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ጨዋታ ፌዴራል ዋና ዳኛ በፀጋው ሽብሩ እንደሚመሩት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ግምታዊ አሠላለፍ
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
ሶሆሆ ሜንሳህ
ብርሀኑ በቀለ – ቃለአብ ውብሸት – ፍሬዘር ካሳ – ኢያሱ ታምሩ
ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን – ተስፋዬ አለባቸው – አበባየሁ ዮሐንስ
ዑመድ ዑኩሪ – ደስታ ዋሚሾ – ፀጋዬ ብርሃኑ
አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል ተሾመ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመንህ ታደሰ – ሳሙኤል አስፈሪ – ያሬድ ሀሰን
ኤልያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኑ – ሙለቀን አዲሱ
እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን