ሰርቢያዊው የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ጉዳዮች ሲነሳ የነበረው የመሰናበታቸው ጉዳይ የተቃረበ ይመስላል።
አንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዘንድሮ የውድድር ዘመን ተጠናክሮ ለመቅረብ በዓመቱ መጀመርያ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፓቲችን መሾሙ ይታወቃል። ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አሰልጣኙ በሚያሳዩት ግትርነት እና ከተጫዋቾች ጋር ያላቸው ተግባቦት ጥሩ አለመሆኑ ሲሰማ የቆየ ሲሆን የክለቡ ቦርድም በዚህ ደስተኛ እንዳልሆነ ተነግሯል።
አሁን ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ዝላትኮ ክራምፓቲች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ የተደረገ ሲሆን ምንም እንኳን በክለቡ በኩል ይፋዊ ማረጋገጫ ባናገኝም ከፈረሰኞቹ ጋር የመለያየታቸው ነገር እርግጥ እየሆነም ይመስላል።
በተያያዘ ዜና ቅዱስ ጊዮርጊስ በስድስተኛው ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታን እንዲያግዝ የተስፋ ቡድኑ አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ ወደ ሀዋሳ እያመራ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በዚህ ጉዳይ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል።