በጉጉት የተጠበቀው የወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማ ጨዋታ ያለግብ ከተጠናቀቀ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።
ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ወላይታ ድቻ
ስለጨዋታው
“የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው በምንፈልገው መንገድ ሄዶልናል ብዬ አላስብም ፋሲል ከነማ ከያዘው የተጫዋች ጥራት አንፃር በድፍረት ኳሶችን መስርተን ለመውጣት አልቻልንም እንደቡድን ተጫዋቾቼ ለጨዋታው ሆነ ለተጋጣሚያችን የሰጡት ግምት ሜዳ ላይ ይታይ ነበር ይሄ ደግሞ መታረም የሚገባው ነው።”
ስለውጤቱ
“ከነበረው ነገር አንፃር በውጤቱ ደስተኞች ነበርን እንደሌላው ጊዜ ከመስመሮች በሚሻሙ እንዲሁም በቆሙ ኳሶች እድሎችን መፍጠር አልቻልንም በማጥቃት ረገድ ዛሬ ጥሩ አልነበርንም።”
በጨዋታው ይዘውት ስለገቡት እቅድ
“ለሁሉም ቡድኖች ክብር ሰጥተን እንጫወታለን እንተናገርኩት አክቡዶ የማየት ነገር ተጫዋቾቻችን ላይ ይታይ ነበር አንዴ ወደ ሜዳ ከገባህ በኃላ ደግሞ የተጫዋቾችን አዕምሮ መቀየር በጣም ከባድ ነው ማጥቃታችን ዛሬ ጥሩ አልነበረም የነበረን ሁለተኛ አማራጭ ተጠቅመን በተለይ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወጣት ተጫዋቾቻችንን አስገብተን በመልሶ ማጥቃት ለማስቆጠር አስበን ነበር ነገርግን ለዋንጫ ፉክክር የሚደረግ ጨዋታ እንደመሆኑ ጥንቃቄ የበዛበትም ስለነበር ውጤቱ ከዛ አንፃር ተገቢ ነው።”
ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ
ስለጨዋታው
“ወደ ደረጃችን ለመመለስ በሙሉ ሀይላችን ያደረግነው ጨዋታ ነበር ስንጀምር በሁለት አጥቂ በመጠቀም የእነሱን የራሳቸውን አቅም ለመጠቀም አስበን ነበር ነገርግን አጥቂዎቹ በቦታው ላይ ከመገኘት ባለፈ በቡድን እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ አልነበራቸውም በሁለተኛው አጋማሽ ግን ለውጥ አድርገናል።ሙሉ ለሙሉ ተጭነናል ወደ ጎል ለመድረስ ያደረግነው ጥረት ጥሩ ነበር ነገርግን ውጤቱ የሚገባን አልነበረም።”
ሦስቱ ቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾችን መጠቀም አለመቻላቸው
“ዛሬም ያስገባነው ቡድን ጥሩ ነገር አለው ነገርግን ያልገቡት ልጆች ቢኖሩ በአጨራረስ ረገድ ሊያግዙን ይችሉ ነበር ፤ በዚህ ደረጃ ቋሚ ተሰላፊዎች ሳይኖሩ እንኳን የቡድኑ ደረጃ ትልቅ የሚባል ነው ከዚህ አንፃር ጥሩ ነው።”