👉🏼 “በእግርኳስ አክብደንም አቅለንም የምናየው ቡድን የለም።”
👉🏼 “ተጫዋቾቼ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠንቅቀው አውቀው የሚጫወቱ ናቸው።”
👉🏼 “አንድ ቡድን ተጫዋች እያፈራረቁ በማጫወት አይሰራም”
👉🏼 “እከሌ ትወጣለች ተብሎ አያሰጋንም አያንበረክከንም።”
በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና የቡድኑ አንበል ናርዶስ ጌትነት ተገኝተዋል። አሰልጣኝ ፍሬው ከቅድመ ዝግጅት አንስቶ ወደ ቦትስዋናን አቅንተው እስከተመለሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሁኔታ በመግቢያ ንግግራቸው እንዲህ ገልፀዋል “በዓለለም ዋንጫ ማጣርያው ሁለተኛ ጨዋታችን ነበር። ከዝግጅት አኳያ ጥሩ ነበር የተዘጋጀነው። በቀን ሁለት ጊዜ ለመዘጋጀት እቅድ የነበረን ቢሆንም ከሴካፋው ከመምጣታችን አንፃር ተጫዋቾች ላይ ድካም ስለነበሩ በቀን አንድ ጊዜ ለመዘጋጀት ተገደናል። በዝግጅት ወቅት ተጫዋቾችቻችን ላይ ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነበር። ነገር ግን የማገገሚያ ጊዜ እጥረት ስለነበረብን የአቅም ማነስ በተጫዋቾቹ ዘንድ ይታይ ነበር። በተረፈ በ35 ሜዳ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተን የአቋም መለኪያም አድርገን ነው ወደ ቦትስዋና የተጓዝነው። ቦትስዋና ከሄድን በኋላ የአየር ሁኔታው ትንሽ ከብዶን ነበር። ከፍተኛ ሙቀት ያለ በመሆኑ ያንን መላመድ አስፈልጎን ነበር። በጨዋታውም 2-0 እስክንመራ ድረስ ጥሩ ብንሄድም አንድ ጎል በራሳችን ስህተት ከተቆጠረብን በኋላ ጫናዎች ነበሩ። ሆኖም በቶሎ ሲስተም ቀይረን ተጨማሪ ጎል በማስቆጠር አሸንፈን ልንወጣ ችለናል።” በማለት ገልፀዋል።
በማስከተል ከሚዲያ ጥያቄዎች ተነስተው መልሶች ተሰጥተዋል
በሴካፋ የነበረው ጠንካራ ጎን በጨዋታው ላይ ስላለመታየቱ
በዚህ ጉዳይ የሁላችንም እይታ ይለያያል። ሴካፋ ላይ ጥሩ ነበርን። ነገር ግን ከፍተኛ ድካም ነበረብን። ይህ ከግምት ሊገባ ይገባል። ከዚህ አንፃር ቦትስዋና ላይ የታየው ነገር ጥሩ ነው። በተጨማሪ እኛ ለሁሉም ቡድን እንደምንዘጋጀው እነሱም እኛን አጥንተው ይመጣሉ። ስለዚህ ጨዋታዎች ቀላል አይሆኑም። ያም ሆኖ በጥሩ መንገድ ተጫውተናል። ጎሎች ያስቆጠርንበት መንገድም ጥሩ ነበር።
ስለ ኚቦኝ የን፣ መሳይ ተመስገን እና ረድኤት አስረሳኸኝ የተለየ አቅም
በእግርኳስ ውስጥ ለእያንዳንዳቸው ለተጫዋቾች የምሰጣቸው ሚናዎች አሉ። በዘመናዊ እግርኳስ ተጫዋች ዘርፍ ብዙ እውቀቶች ያስፈልጋሉ። በሜዳ ውስጥ ምን መስራት እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው። አንዳንዴ አሰልጣኝ ከሚሰጣቸው ሚና ውጭ በራሳቸው አቅም ጎልተው የሚወጡ ልጆች አሉ። ለምሳሌ ሦስቱ ልጆች በዚህ መንገድ ነው የማያቸው በተለይ ኒቦኝ ላይ እንደ ባለሙያ ብዙ ደክሜባት ያመጣኋት ልጅ ናት። ወደፊትም ሀገሯን በሚገባ የምታገለግል ልጅ ናት። በአጠቃላይ ግን ሌሎችም እያንዳዶቹ ተጫዋቾች በየቦታቸው እግርኳስ ገብቷቸው የሚጫወቱ ናቸው። ተጫዋቾቼ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠንቅቀው አውቀው የሚጫወቱ ልጆች እንዳሉኝ መግለፅ እፈልጋለሁ።
ቦትስዋናን አክብደው ስለመግባታቸው
እኔ ጥያቄው አቅላችሁ ገባችሁ የሚል መሆኑን ነበር የሰማሁት። አክብዳቹ ከተባለ በእግርኳስ አክብደንም አቅለንም የምናይው ቡድን የለም። ለተጫዋቾቻችን ከምንሰጣቸው ነገሮች አንዱ እግርኳስ ወቅታዊ አቋም መሆኑን ብቻ ነው። እንዳውም እነርሱ እኛን አክብደው ወደ ሜዳ እንደገቡ በተለያዩ ነገሮች መመልከት ችለናል።
የወዳጅነት ጨዋታን በተመለከተ
ከፌዴሬሽኑ ጋር እየተነጋገርን ነው። በቀጣይ ይህ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ያስፈልገዋል እንጠይቃለን። ፌዴሬሸኑ እስካሁን የምንጠይቃቸው ብዙ ነገሮች በሚገባ እየመለሰልን ስለሆነ አሁንም የወዳጅነት ጨዋታ ያስፈልገናል።
የመልስ ጨዋታውን በሚያደርጉበት አበበ ቢቂላ ልምምድ ስለመስራት
አያት ያለው የካፍ ልህቀት ማዕከል ሜዳ ለልምምድ ምቹ ባለመሆኑ ሀገርን በመውደድ እንደ ሀገር አስበው በነፃ ሜዳውን ፈቅደውልን በ35 ሜዳ ለጊዜው እየሰራን እንገኛለን። በዚህ አጋጣሚ ፈቃጆቹን አመሰግናለው። እንደ የአስፈላጊነቱ ጨዋታውን በምናደርግበት አበበ ቢቂላ ሜዳ ለመስራት የምንችልበት ዕቅድ አውጥተን እየሰራን እንገኛለን።
ስለ ቡድኑ ዕድገት
በጣም ከፍተኛ እድገት አለ። አንድ ቡድን ተጫዋች እያፈራረቁ በማጫወት አይሰራም። ያሉን ተጫዋቾች ወጥ ናቸው። ያም ቢሆን እግርኳስ ብዙ ነባራዊ ሁኔታዎች ይኖሩታል። ጉዳት ቅጣት እና የአቋም መውረድ ይኖራል። ይህን እያየን የምናካትታቸው ተጫዋቾች ይኖራሉ። ቡድኑ እድገት አለው ። ጨዋታዎች ሲያልቁ እኔም ተጫዋቾቼ እራሳችንን እንገመግባለን። በአጠቃላይ ቡድኔ ላይ መሻሻሎች እድገቶች እያየው ነው። ጎሎች ከሜዳም ውጭ በሜዳም የምናስቆጥረው መጠን ከአንድ ጎል ከፍ እያለ ነው። ይህም ቢሆን እግርኳስ ስህተት አለው፤ በሚቀሩን ነገሮች እያስተካከልን እንሄዳለን።
የቡድኑ ቀጣይ ዕቅድ
የቡድኑን ዕቅድ በተመለከተ ቡድኑ በደንብ በእቅድ የተሰራ ነው። የሙያም ሆነ የተጫዋቾች ዕቅድ አለን። እኔ የመጀመርያው ዕቅዴ ሩዋንዳ ላይ ለዓለም ዋንጫው ቀጣይ ያጣርያ ዙር ማለፍ ነበር፤ አሳክተናል። በማስከተል የሴካፋ ዋንጫ መጣ፤ እርሱንም ሻምፒዮን ሆነን ተመልሰናል። አሁን ከፊታችን የሚጠብቀን ስራ አለ፤ እርሱን አቅደን እየሰራን ነው። ዕድሜን በተመለከተ እከሌ በፓስፖርት ምክንያት ይወጣል የሚለው ይህ የእኛ ሥራ ነው። የምንሥራውን ጠንቅቀን እናውቃለን። ፓስፖርት አይተን መጫወት የሚያስችለውን እና የማያስችለውን እንለያለን። እከሌ ትወጣለች የሚል ነገር እኛን አያሰጋንም፤ አያንበረክከነም። ሌላ ትውልድ አለ፤ ወላድ በድባብ ትሂድ።