ባህር ዳር እና ወላይታ ድቻን ያገናኘው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ አራት ግቦች ተስተናግደውበት የጣና ሞገዶቹን ባለ ድል አድርጎ ተደምድሟል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ጅማ አባጅፋርን ሁለት ለምንም ያሸነፉት ባህር ዳሮች ከመጨረሻው ጨዋታቸው አንድም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በትናንትናው ዕለት የሊጉን መሪነት ከተረከባቸው ፋሲል ጋር ተጫውተው ነጥብ ከተጋሩበት ፍልሚያ እድሪስ ሰዒድን ብቻ በአበባየሁ አቺሶ ለውጠው ጨዋታውን ቀርበዋል።
ኳስን በተሻለ በመቆጣጠር መጫወት የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች በ6ኛው ደቂቃ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም የቀኝ መስመር ተከላካዩ ግርማ ዲሳሳ መሬት ለመሬት የላከውን ኳስ የዘገየ የሳጥን ውስጥ ሩጫ ያደረገው አብዱልከሪም ንኪም በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ቢመታውም የግብ ዘቡ ፅዮን መርዕድ አምክኖበታል። ወላይታ ድቻዎች በአንፃሩ በአመዛኙ ወደ ራሳቸው ሜዳ በመጠጋት የባህር ዳር የኳስ ቁጥጥር አደጋ እንዳያመጣ ሲጥሩ ነበር። ከዚህ ውጪ የሚያገኟቸውን ኳሶች በረጅሙ በመላክ ግብ ለማግኘት ታትረዋል።
ጨዋታው 18ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም በጨዋታው የተሻለ የጨዋታ ቁጥጥር ብልጫ የነበረው ባህር ዳር ወደ መሪነት ተሸጋግሯል። በዚህም ከቅጣት ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ከዐየር ላይ አበባየሁ አጪሶ እና ኦሴ ማውሊ ለማብረድ ሲጥሩ ከሳጥኑ ውጪ የነበረው ፍፁም ዓለሙ አግኝቶት በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎታል። ካልተጠበቀ አጋጣሚ ግብ ያስተናገዱት ወላይታ ድቻዎች በአምስት ደቂቃዎች ውስጥ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። በቅድሚያም ቃልኪዳን ከሀብታሙ የደረሰውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል በመገኘት ሲሞክር ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ስንታየሁ ከምንይሉ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ነበር።
በቀጣዮቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ሁለቱ ቡድኖች የተመጣጠነ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ባህር ዳሮች ወደ ጎል በመድረሱ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። በ38ኛው ደቂቃም በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ዲቻ የግብ ክልል ደርሰው መሪነታቸውን አሳድገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የመጀመሪያውን ጎል ያስቆጠረው ፍፁም ከማውሊ በጥሩ ሁኔታ የተነሳውን ኳስ ከተከላካዮች ፈጥኖ በማግኘት በቀኝ እግሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል። አጋማሹ ሊገባደድ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ ወላይታ ድቻዎች ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ጎል አግኝተዋል። በዚህም ከመሀል የተነሳውን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ በግንባሩ ሳጥን ውስጥ እንዲገባ ካደረገው በኋላ ስንታየሁ ሰውነቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን ሲሸፍንለት ፈጥኖ በማግኘት ፋሲል መረብ ላይ አሳርፎታል። የመጀመሪያው አጋማሽም ሦስት ግቦች ተስተናግደውበት ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገው ንኪማ በዚህኛውም ክፍለ ጊዜም የመጀመሪያውን ጥቃት የፈፀመ ተጫዋች ነው። በዚህም በ48ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በራሱ የቡድን አጋር ፍፁም ተጨርፎ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከደቂቃ በኋላ ደግሞ አበባየሁን ቀይሮ በአጋማሹ ወደ ሜዳ የገባው እድሪስ ከርቀት ቡድኑን አቻ ሊያደርግ ነበር። በ57ኛው ደቂቃ ደግሞ ከቀኝ መስመር በተነሳ ኳስ ቡድኑ (ዲቻ) እጅግ ወደ ግብ ቀርቦ ነበር።
በእጃቸው የገባውን ሦስት ነጥብ በማስጠበቅ ውስጥ ሆነው አሁንም ጥቃት መሰንዘር የቀጠሉት የጣናው ሞገዶቹ በ60ኛው ደቂቃ በፍፁም አማካኝነት ሌላ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። በ62ኛው ደቂቃ ግን አምበላቸው አህመድ ረሺድ በሰራው ጥፋት ተቀጥተው አቻ ሊሆኑ ከጫፍ ደርሰው ነበር። በዚህም ተከላካዩ ለግብ ጠባቂው ፋሲል አቀብላለው ያለው ኳስ አጭር ሆኖ የደረሰው እድሪስ በፍጥነት ኳሱን ለስንታየሁ ቢሰጠውም ቁመታሙ አጥቂ እጅግ በአስቆጪ ሁኔታ እንደ ስጦታ የሚቆጠረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ባህር ዳሮች ይህንን ስህተት በተሳሳቱ በሦስተኛው ደቂቃ ግን ሦስተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም በጨዋታው ደምቆ የታየው ፍፁም ዓለሙ በተከላካዮች መሐል ለዓሊ ሱሌይማን ያመቻቸውን ኳስ ፈጣኑ አጥቂ ደርሶበት በግራ እግሩ ሦስተኛ ግብ አድርጎታል።
በሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ መጠነኛ መሻሻል ያሳዩት የጦና ንቦቹ በቀጥተኛ አጨዋወት እና በቆሙ ኳሶች የባህር ዳርን የኋላ መስመር መጎብኘት ይዘዋል። ይህ ቢሆንም ግን ሰብሮ መግባት ተስኗቸዋል። ባህር ዳሮችም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ከኳስ ጋር በመሸሸግ ግባቸውን ላለማስደፈር ጥረው ጨዋታውን ሦስት ለአንድ አሸንፈው ወተዋል።
በውጤቱ መሠረት ባህር ዳር ከተማ ነጥቡን 13 በማድረስ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ሲል ወላይታ ድቻ ደግሞ ከባህር ዳር ጋር ተመሳሳይ ነጥብ ቢኖረውም በግብ ክፍያ ተበልጦ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ተንሸራቷል።